AMN-ታህሣሥ 7/2017 ዓ.ም
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ማካሄድ ጀምሯል።
የምክክር መድረኩ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ተከናውኗል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) በመክፈቻ መርሃግብሩ ላይ እንዳሉት ኮሚሽኑ በእስካሁን ቆይታው በዘጠኝ ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ልየታ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።
ኦሮሚያን ጨምሮ በ971 የኢትዮጵያ ወረዳዎች የተሳታፊዎች ልይታ መከናወኑም ዋና ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
በቀጣይ በአማራ እና በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ለመጀመር ኮሚሽኑ ዝግጅት ማጠናቀቁንም ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስታውቀዋል።
ወቅታዊ ችግሮችን ዘላቂ በሆነ መንገድ በመፍታት አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር እንዲሁም ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በስኬት እንዲቋጭ የተወካዮች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ስለመሆኑም ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ፣ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ማዳበር እንደሚያስችል የተለያዩ ኮሚሽነሮች ተናግረዋል።
በካሳሁን አንዱዓለም