በአማራ ክልል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተጀመረ

You are currently viewing በአማራ ክልል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተጀመረ

AMN – ሚያዝያ 2/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የማህበረሰብ ተወካዮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ የክልል ባለድርሻ አካላት ምክከር ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ከ4 ሺ 500 በላይ የማህበረሰብ ተወካዮች ከመጋቢት 27 እስከ ሚያዚያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ሀገራዊ መግባባት ሊደረስባቸው ይገባል ያሏቸውን አጀንዳዎች በማንሳት 270 ተወካዮቻቸውን መርጠው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

የማህበረሰብ ተወካዮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ የክልል ባለድርሻ አካላት ማለትም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የክልሉ የመንግስት አካላት፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና የተቋማትና የማህበራት ተወካዮች በመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ መግባባት ሊደረስባቸው ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ መምከር ጀምረዋል።

በዚህ የምክክር ምዕራፍ ላይ ከ2 ሺህ በላይ ግለሰቦች እየተሳተፉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

በክልሉ ታጥቀው ጫካ የገቡ አካላት ባሉበት ምክክር ማካሄድ አግባብ ስላለመሆኑ የሚሰጡ አስተያየቶች መኖራቸውን በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአማራ ክልል አስተባባሪ ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት አቶ መላኩ ወልደማርያም አስታውሰዋል።

ይሄ ግን የተሳሳተ እሳቤ ነው ያሉት ኮሚሽነር መላኩ፣ በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ብቻ ሳይሆኑ በእስር ቤት ያሉ ዜጎች ጭምር በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ተወካዮቻቸውን ቢልኩ ኮሚሽኑ በአግባቡ ተቀብሎ ሀሳባቸውን ለማስተናገድ ዝግጁ ስለመሆኑ ጥሪ ያቀረቡት ደግሞ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ናቸው።

የምክክሩ ተሳታፊዎች በቀጣዮቹ ቀናት ከ270 የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በመምከር የአማራ ክልል አጀንዳዎችን ለይተው ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያስረክቡ ይሆናል።

በካሳሁን አንዱዓለም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review