የአውስትራሊያ ራዲዮ ኔትወርክ ክፍል የሆነ አንድ ራዲዮ ጣቢያ በድብቅ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለፕሮግራም አቅራቢነት በመጠቀሙ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
CADA የተባለው የአውስትራሊያ የራዲዮ ጣቢያ ለስድስት ወራት ያህል ለአድማጭ ሳይገልፅ ” “ታይ” የተባለች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ድምፅን ለፕሮግራም አቅራቢነት ሲጠቀም ቆይቷል።
ጣቢያው የኤ አይ ድምፁን የፈጠረው ElevenLabs የተሰኘ ሶፍትዌርን በመጠቀም ሲሆን በየቀኑ ለአራት ሰዓታት የሚቆይ “የስራ ቀናት ከታይ ጋር” የሚል ፕሮግራም ያቀርብ ነበር።

አድማጮች የታይን ተመሳሳይ የድምፅ ዘዬዎችን ማስተዋል ሲጀምሩ ጥርጣሬያቸው እየጨመረ ይመጣል። ምንም አይነት በታይ ስም የተመዘገበ መረጃ አለመኖሩም ጥርጣሬውን እንዲጨምር ያደርገዋል። በመጨረሻም የአውስትራሊያ ራዲዮ ኔትወርክ አዳዲስ የስርጭት ቴክኖሎጂዎችን ለመፈተሽ ይህንን እንዳደረገ ይፋ አድርጓል።
በሬዲዮ ስርጭት ውስጥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን መጠቀምን የሚከለክሉ ምንም አይነት ወቅታዊ ህጎች ባይኖሩም እርምጃው ታዳሚዎችን በማሳሳቱ እና እውነታው ግልፅ አለመደረጉ በጣቢያው ላይ ተቃውሞን አስነስቶበታል። የድምፅ ተዋንያን ቡድኖችም በዚህ ረገድ የበለጠ ታማኝነት እና ቁጥጥር እንዲደረግ ጠይቀዋል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
በሊያት ካሳሁን