በአዲሱ ዓመት የጎብኚዎች ቀዳሚ መዳረሻ ሀገራት

You are currently viewing በአዲሱ ዓመት የጎብኚዎች ቀዳሚ መዳረሻ ሀገራት

አፍሪካ ማራኪ መልክዓ ምድር፣ የበለፀጉ ባህሎች እና ቅርሶች መገኛ ምድር ነች፡፡ ልብን በሃሴት የሚሞሉ ተራሮች እና የዱር እንስሳት ሞልተዋል። ጫካዎችን፣ ተራሮችንና ሜዳዎችን አቆራርጠው የሚፈሱ ወንዞች፣ የታሪካዊ  አሻራን የሚያንጸባርቁ ህንጻዎች፣ ቀልብን የሚይዙ የባህር ዳርቻ  መዝናኛዎች፣ፓርኮች፣ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ሁሉ በአፍሪካ ይገኛሉ፡፡ አፍሪካ ከሰው ሰራሽ እስከ ተፈጥሮ ሃብት ድረስ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ ሁሉም አይነት ስጦታ አላት። ታባ አፍሪካ ሳፋሪስ የተባለ ገጸ-ድር ከሰሞኑ በመጪው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጎብኘት ያለባቸው የአፍሪካ ሀገራትን ይፋ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ

ታባ አፍሪካ ሳፋሪስ ገጸ-ድር በፈረንጆቹ 2025 አስደሳች ጊዜን፣ ጀብዱ የተሞላባቸው ጉብኝቶችን እና የማይረሳ ትውስታን መፍጠር ለሚፈልጉ ተጓዦች መጎብኘት አለባቸው ያላቸውን ሀገራት ይፋ ባደረገበት መረጃው ከተጠቀሱት ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡

ገጸ-ድሩ “Where to Visit in Africa in 2025” ሲል ባጋራው ጽሑፍ  ኢትዮጵያ ቀልብን የሚስቡ የጥንታዊ ታሪክ እና አስደናቂ መልክዓ ምድር መገኛ ምድር ነች ይላል፡፡ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዘመን የማይሽራቸው የእምነት እና የጥበብ ምስክሮች ሆነው ይታያሉ የሚለው መረጃው ግርማ ሞገስ የተላበሱ የጎንደር ኪነ-ህንጻዎች (የፋሲል ግንብ) መጎብኘት ያለባቸው ስፍራዎች ናቸው ይላል፡፡

በእግር መጓዝ ለሚፈልጉ ቱሪስቶች በሁሉም አካባቢ ፓርኮች ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ እና ልዩ ጣእም ያላቸው ምግቦችን ማጣጣም ለሚፈልጉም ምርጫው ብዙ ነው፡፡ ማህበረሰቡ በአጠቃላይ እንግዳ ተቀባይ መሆኑ ሃገሪቱን ለጉብኝት ተመራጭ ያደርጋታል ሲል ያክላል፡፡

ጥንታዊ ታሪኮች፣ የተፈጥሮ መልክዓ ምድር እና የማህበረሰቡ እንግዳ አክባሪነት ነፍስን  የሚመግብ እና ምናብን በጉጉት የሚያንጠለጥል ነው የሚለው ይህ ገጸ-ድር  በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ጉዞ ማራኪ እና አስደሳች ትውስታ የሚቀረጽበት ነው ይላል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ጥንታዊ ቅርሶችና በቅርቡ የተገነቡ አዳዲስ መዳረሻዎች ለኢትዮጵያ ሌላ ገጽታ ከማላበስ አልፈው በቱሪስቶች ዘንድ ተመራጭ አድርጓታል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም፣ የአንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ እንጦጦ ፓርክ እና በኮሪደር ልማቱ የተሰሩ እና እየተሰሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን የጎብኝዎች መሸጋገሪያ ሳይሆን መዳረሻ አድርገዋታል፡፡ እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪና ኮይሻን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ከታሪካዊ መዳረሻዎች ጋር ተዳምረው የቱሪስቶችን ቆይታ ከማራዘም ባለፈም ኢትዮጵያ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ደቡብ አፍሪካ

ቱሪስቶች በደቡብ አፍሪካ

ደቡብ አፍሪካ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚገኙባት ሀገር ነች፡፡ ከውብ ከተሞች እስከ ትልልቅ ሜዳዎችና የዱር አራዊት የተሞሉ ፓርኮች መገኛም ነች፡፡ ይህ አይነቱ ልዩ  መዳረሻ ተጓዦች የበለጠ ዓለምን እንዲያስሱ፣ እንዲዝናኑ፣ ከሌላ ማህበረሰብ ጋር እንዲገናኙ እና እንዲነቃቁ ያደርጋል ይላል ገጸ ድሩ። በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ በሚያስደንቅ መልክዓ ምድሯ፣ የበለጸጉ ባህሎቿ እና በማይረሱ ትዝታዎቿ ምንነት በጎብኝዎች ትወደዳለች ይላል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ልዩ ልዩ ህብረ-ቀለም ያላቸው ዕፅዋቶችና አዕዋፋት በስፋት ይገኛሉ፡፡ የሃገሪቱ የባህር ዳርቻዎች ውብ እና ነፋሻማ ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ በአብዛኛው የምትታወቀው በፀሃያማ የአየር ንብረቷ ሲሆን፣ ጎብኚዎች ዝናባማ ወራቶች እስኪያልፉ ድረስ ወደዚህች ሃገር ሄደው የሚዝናኑባት የቱሪስት መዳረሻዎች እንደሆኑም ከላይ ከተጠቀሰው ገጸ-ድር በተጨማሪ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ሞሮኮ

ጎብኚዎች በሞሮኮ ጥንታዊ ከተማ

ሞሮኮ ለመገኘት እና ሀገሪቱን ለመጎብኘት የማይጓጓ ቱሪስት የለም፡፡ ዋና ከተማዋ ሳቢ ናት፡፡ የተረጋጋው የሠሃራ በረሃማ  ቦታ ደግሞ አስደናቂ እና የጀብዱ ስሜትን የሚፈጥር ነው። በጥንታዊ ከተሞች ደግሞ ታሪክ ህያው ሆኖ ቆሟል፡፡ እያንዳንዱ  መንገድ ያለፈውን ታሪክ  ይናገራል። ልዩ  ጣዕም ያላቸው ምግቦች በዘመናዊ እና ባህላዊ ሆቴሎች ይቀርባሉ፡፡ ግርማ ሞገስ የተላበሱ ግመሎችን ወደ በረሃው እምብርት እየጋለቡ፣ ከፊት የተዘረጋውን ወርቃማ አሸዋ ማቋረጥ የሚፈጥረው ስሜት ድንቅ ነው ይላል ገጸ-ድሩ። እንደ ኢሳውራ ያሉ የባህር ዳርቻ ከተሞች፣ አስደናቂ እይታቸው እና ጥበባዊ መንፈሳቸው ጎብኚዎችን ይስባል ሲልም ያክላል፡፡ በዚህም በአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት የማይረሳ ጊዜ ለማለፍ እና ማራኪ ጉዞ ለማድረግ ሞሮኮ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ተብላለች፡፡

በአጠቃላይ በአፍሪካ የሚጎበኙ ሃብቶች እና ቅርሶች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ኤፍ ቲ ኤን ኒውስ “7 Emerging Travel Destinations in Africa for 2024” በሚል ባወጣው መረጃ” አፍሪካ ወሰን የለሽ የሚጎበኝ ሃብት እና የደመቁ ባህሎች ያላት አህጉር ነች”፡፡ በተጨማሪም “አፍሪካ ሰፊው ዓለም ገና እየሰማቸው እና እያያቸው ያሉ፣ ወደፊትም የሚያያቸውና የሚሰማቸው ድንቅ ባህሎችና ቦታዎች መገኛ ነች” ሲል ይገልጻታል፡፡

ቦትስዋና

ቦትስዋና በአስደናቂ የብዝሀ ህይወት ትታወቃለች፡፡ ይህም ለዱር አራዊት አድናቂዎች የመዳረሻ ገነት ያደርጋታል። የኦካቫንጎ ዴልታ እና  የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ቦታዎች በጣም ልዩ ከሆኑ የጎብኝዎች መዳረሻነት መካከል ተጠቃሾች ናቸው። በዱር አራዊት የተሞሉ፣ በጫካዎች የተሸፈኑ ጠመዝማዛ ወንዞች መገኛቸው በቦትስዋና ነው፡፡ የቾቤ ብሔራዊ ፓርክ እና የቃላሃሪ በረሃ የሀገሪቱን የሥነ-ምህዳር ውበት ገላጭ እና አስደናቂ መልክዓ ምድሮች ናቸው፡፡ በዚህም በታባ አፍሪካ ሳፋሪስ ገጸ-ድር መጎብኘት አለባቸው ከተባሉ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ተካትታለች፡፡

ዚምባብዌ

ዚምባብዌ በተፈጥሮ ውበት እና በባህል ብዝሃነት ያሸበረቀች ሀገር መሆኗ ይነገራል፡፡ ይህን ደግሞ በተለያየ ጊዜ ሀገሪቱን የጎበኙ ቱሪስቶች የሚመሰክሩት ነው፡፡ በጎብኝዎች የሚመረጠው  የቪክቶሪያ ፏፏቴ የሚያስደንቅ ስሜት ይፈጥራል። ግርማ ሞገስ የተላበሱ የዱር አራዊት በተፈጥሮ መኖሪያቸው ማለትም በሁዋንግ ብሔራዊ ፓርክ ይገኛሉ፡፡ የበለፀገ ጥንታዊ የስልጣኔ ታሪኮችን የሚዘክሩ ህንጻዎችና ሐውልቶችም በዋና ከተማዋ ይገኛሉ፡፡ ሃገሪቱ  ለጎብኚዎች ብዙ መዳረሻ ማቅረብ የምትችል መሆኗን ገጸ-ድሩ ጠቁሟል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review