
AMN-ታህሣሥ 15/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና በሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የተሰሩ የሪፎርም ስራዎች በከተማ ደረጃ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን እና ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሚያስችል ልምድ ሊቀሰምበት የሚችል መሆኑን የተቋማቱን የሪፎርም ስራዎች የጎበኙ አመራሮች ተናገሩ።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት አዘጋጅነት በሪፎርሙ ስኬታማ የሆኑ ተቋማትን ልምድ ለመቅሰምና ለማስፋት የሚያስችል የከተማው ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።
የከተማው አስተዳደር የተቋም ግንባታን ቁልፍ ተግባሩ በማድረግ 16 ተቋማት ተለይተው ወደ ሪፎርም እንዲገቡ እና አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሚያስችል ስራ ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል።
በዚህ ውስጥ ስኬታማ የሆኑት የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ እና የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የሰሯቸው የሪፎርም ስራዎች እንደከተማም ብሎም እንደሀገር ተሞክሮ የሚቀሰምባቸው በመሆኑ የከተማው አመራሮች ልምዶችን እንዲቀስሙ እና ወደ ተቋሞቻቸው እንዲያሰፉ እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
ከተቋማቶቹ የቀስምናቸው ተሞክሮዎች በየተቋሞቻችን በማስፋት አገልግሎትን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ቀልጣፋ አገልግለ እንዲሰጥ ያስችለናል ብለዋል አመራሮቹ።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን መታገል ብሎም የተገልጋይ እርካታን ማሳደግ እንደሚቻል መመልከታቸውንም አመራሮቹ ተናግረዋል።
በሰብስቤ ባዩ