በአዲስ አበባ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን፣የህዝብ ትራንስፖርት እና ተቋማትን ከትምባሆ ነፃ ማድረግ ተችሏል፡- የአዲስ አበባ ምግብ እና መድሃኒት ባለስልጣን

AMN – ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ትምባሆ ማጨስ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን፣የህዝብ ትራንስፖርት እና ተቋማትን ከትምባሆ ነፃ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ምግብ እና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ ፡፡

ባለስልጣኑ ይህንኑ ስራ አጠናክሮ ለመቀጠል ባለፉት 5 ወራት የሰራቸዉን ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል፡፡

ባለስልጣኑ የግንዛቤ እና የቁጥጥር ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቁሟል፡፡

በአዲስ አበባ ትምባሆ ማጨስ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች ከትምባሆ ነፃ የሆኑ ተቋማትን መፍጠር እንደተቻለ ባለስልጣኑ ተናግሯል፡፡

በቀጣይም የተጀመሩ ስራዎችን በማሰቀጠል ጤናማ ማህበረሰብ የመፍጠር ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል፡፡

በፈረንጆቹ 2016 በኢትዮጵያ በተጠና ጥናት 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን አጫሾች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚሆኑት በየቀኑ የሚያጨሱ ናቸዉ፡፡

በዚህም ምክንያት በየዓመቱ 17 ሺህ ሰዎች ለሞት እንድሚዳረጉም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡

እንደ ጥናቶች ከሆነ በሲጋር ዉስጥ ከ7 ሺህ በላይ ኬሚካሎች ያሉ ሲሆን 70 የሚሆኑት ቀጥታ ለካንሰር የሚያጋልጡ ናቸው፡፡

በትምባሆ ምክንያት በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ8 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለሞት እንደሚዳረጉም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በቴዎድሮስ ይሳ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review