በአዲስ አበባ የተሰሩ እና እየተሰሩ ያሉ ሰው ተኮር ስራዎች የሚደነቁ ናቸው-የምክር ቤት አባላት

You are currently viewing በአዲስ አበባ የተሰሩ እና እየተሰሩ ያሉ ሰው ተኮር ስራዎች የሚደነቁ ናቸው-የምክር ቤት አባላት

AMN-መጋቢት 11/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የተሰሩ እና እየተሰሩ ያሉ ሰው ተኮር ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን የህዝብ ተወካዮች የምክር ቤት አባላት ተናገሩ፡፡

የምክር ቤት አባላት በፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት አፈፃፀምን መነሻ በማድረግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥያቄዎች እና አስተያየት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ወደ ብልጽግና እየሄደች ያለችበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በአዲስ አበባ እየተሰሩ ያሉ እና የተሰሩ ሰው ተኮር ስራዎች መጪውን ትውልድ ማዕከል ያደረጉ በመሆናቸው በሌሎች አካባቢዎችም ሊስፋፋ ይገባል ብለዋል፡፡

በመዲናዋ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ለነዋሪዎች የተሻለ አኗኗር የፈጠረ መሆኑን የገለጹት አባላቱ ለኑሮ ምቹ ባልነበረ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ማህበራዊ መስተጋብራቸው ሳይነካ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መዘዋወራቸው የሚያኮራ ስራ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ለአብነትም በካሳንችስ መልሶ ማልማት እና ኮሪደር ልማት፤ ከካሳንችስ ለተነሱ ነዋሪዎች በገላን ጉራ የተሰሩ ትምህርት ቤቶች፤ የንግድ ማእከላት ፤የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች እና የሴቶች ስራ እድል ፈጠራ የሚደነቅ ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የገላን ጉራ ነዋሪዎች የተሻለ አካባቢ እና ኑሮ ተፈጥሮላቸው እየኖሩ መሆኑን መመልከታቸውንም አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በመንገድ ማሳለጥ በቦሌ ቡልቡላ ፓርክ በከተማ መስፋፋት ምክንያት የተፈናቀሉ ገበሬዎችን መልሶ ለማቋቋም የተሰራው የቃሊቲ እንስሳት ልማትና ግብርና ልህቀት ማዕከል የኑሮ ውድነትን ታሳቢ ያደረገ የገበያ ማእከል በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ሌላኛው ስኬት መሆኑን እና እንደ ሀገር ሊሰፋ የሚገባው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጠንካራ መንግስት ጠንካራ ተቋም ይገነባል ያሉት የምክር ቤት አባላት አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል እና ስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና ያላቸው ተቋማት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን የተጀመሩ ስራዎች ታሪክ የማይረሳው እና ዘመን ተሻጋሪ ትውልድ የሚኮራበት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡ይህንንም እንደ ሀገር ማስፋትና ማጽናት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት፡፡

ለልማት ስራዎቹ መሳካት ያላሰለሰ ጥረት ላደረጉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በስራዎቹ ውስጥ ለተሳተፉ አመራሮች በሙሉ የምክር ቤት አባላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review