AMN – ጥር 20/2017 ዓ.ም
በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ማሳካት የሚያስችሉ በጎ ጅምሮች እየተስተዋሉ ነው ሲሉ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ገለጹ፡፡
አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ የብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ኢብራሂም በማብራሪያቸው አሁን ላይ ስጋት ተብለው ከሚነሱ ጉዳዮች ውስጥ ከተዛቡ ትርክቶች የመነጩ እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶችን ማረም ይገባል ሲሉም አመልክተዋል፡፡
እነዚህ ችግሮች አገሪቱ የጀመረችውን ሁለንተናዊ ብልጽግና በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የራሳቸው አሉታዊ ጎን ስላላቸው በፍጥነት ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጥል እንዳለባቸው ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ምህዳሩ የጠበበበት ፤ሰው በፖለቲካ አመለካከቱ የሚታሰርበት፤ከአገር ተሰዶ በሌላ አገር በስደት የሚኖርበት ፤የሀሳብ ነጸነት የማይከበርበት ፤ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የማይከበሩበት ሁኔታ እንደነበር ያመለከቱት አቶ ኢብራሂም ብልጽግና ሲወለድ እነዚህን ሁሉ እዳዎች ተሸክሞ ነው የመጣው ብለዋል፡፡
በዚህም የለውጡ መንግስት የመጀመሪያ እርጃ የነበረው እነዚህን እዳዎች ማስተካከል ነበር ብለዋል፡፡
የፖለቲካውን ምህዳር ማስፋት፤ ማንኛውም ሰው ያለውን አማራጭ ሀሳብ ይዞ መጥቶ በፖለቲካው መድረክ እንዲሳተፍ መደረጉን የገለጹት ኃላፊው ከዚህ ቀደም በስደት የነበሩ በርካታ የፖለቲካ ተዋናዮች ወደ ሀገር መምጣታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የዜጎች እስር ቤት ተብላ የነበረችን ሀገር አብዛኛውን እስር ቤት ነጻ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው ፓርቲ ለዜጎች እኩል መብት ያልሰጠ ፤ገዢ እና ደጋፊ በሚል ስም ከፋፋይ ነበር ያሉት አቶ ኢብራሂም አሁን በመጣው ለውጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩል የሚሳተፉበት ፓርቲ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር የጎደለውን የዲሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ ሰፊ ስራ መሰራቱንም አመልክተዋል፡፡
የዲሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ የማድረግ ስራ ተሰርቷል ያሉት ኃላፊው በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን እና በሽግግር ፍትህ በኩል ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም በየትኛውም ስርአት ያልተሞከረ ትልቅ ስራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ሰላምን በማጽናት ረገድ ከተሰሩ ስራዎች የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለአብነት ያነሱት አቶ ኢብራሂም አሁንም ከሸኔ ጋር የተደረሰው ስምምነት እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጉሙዝ ሀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ የተደረገበት አግባብ አበረታች ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እና የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በሰለሞን በቀለ