የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ደህንነት ዙሪያ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት እድርገዋል።
ሚኒስትሩ በተለይ በቅርብ ጊዜ በባቡሩ ኤሌክትሪክ መስመር ላይ ጉዳት እና ስርቆት መድረሱን ተከትሎ ችግሩን ለመፍታት ከአካባቢው ሃይማኖት አባቶች፣ ከጎሳ መሪዎች፣ ከፀጥታ አካላት እና ከተለያዩ ስራ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታትና ባቡሩን በሙሉ አቅም መጠቀም እንዲቻል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ችግሩ እንዲፈጠር ያደረጉ አካላትን በትብብር የማጥራት ስራ መከናወን እዳለበት ገልጸዋል።
በባቡር መስመሩ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከፌዴራል መንግስት፣ ከክልል መንግስታት፣ ከፀጥታ አካላት፣ ከኢትዮጵያ መብራት ሀይል እና ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በባቡር መስመሩ ላይ ጉዳት በማድረስ ስርቆት በሚፈፅሙ አካላት ላይ ከመንግሥት ጎን በመሆን የማጋለጥ ስራ እያከናወኑ መሆኑን መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።