በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ተካሄደ የሚባለው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሲሳተፉበት ነው- ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)

AMN – ኅዳር 7/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአራቱም የትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች ከመጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብ አባላት ጋር በአዲስ አበባ ተወያይቷል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) “በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ተካሄደ የሚባለው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሲሳተፉበት ነው” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ምክክር የትግራይ ክልል በምክክሩ የሚሳተፍበትን ሁኔታ ለመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ትግራይ ክልልን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ አሳታፊና አካታች ምክክር ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የክልሉ ህዝብ ሃሳቦች ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች በጥያቄ እና በአስተያየት መልክ አቅርበዋል፡፡

ኮሚሽኑ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እንደ ድልድይ ሆኖ በማገልገል ሚናውን እንዲወጣም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡

መንግስት የትግራይ ክልል ህዝብ ችግሮችን ትኩረት ሰጥቶ እንዲፈታ ኮሚሽኑ ጫና ማድረግ እንደሚኖርበትም አክለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ምክክር ለማድረግ መጀመሪያ መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ተሳታፊዎቹ ለዚህም ህዝቡ የሚሰማውን ግልፅ አድርጎ የሚናገርበት መድረክ ሊመቻችለት ይገባል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ እንደ ገለልተኛ ተቋም ህዝቡ ጋር ወርዶ በማወያየት ያጋጠሙ ችግሮች እንዲፈቱ የሚያስችል ከሆነ በትግራይ ክልል የምክክሩን ሂደቶች ለማካሄድ መንገድ እንደሚከፍትለትም ነው ተሳታፊዎቹ የጠቆሙት፡፡

በመድረኩ የተገኙ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮችም ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዛሬ በተካሄደው ውይይት ከመቀሌ፣ ከአክሱም፣ ከአዲግራት እና ከራያ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ75 በላይ የሚሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብ አባላት መሳተፋቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review