በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ኢኒሼቲቮች የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከማሳለጥ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ተገለጸ

AMN- ግንቦት 11/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ኢኒሼቲቮች የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከማሳለጥ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ተናገሩ።

20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት በሥራ ላይ የተመሰረተ የባለሙያዎች አህጉራዊ ስብሰባ “የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች” በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

በስብሰባው የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።

ከስብሰባው ጎን ለጎንም ሀገራት በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ያላቸውን ተሞክሮ የሚለዋወጡበት የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት በመዘርጋትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድ ስኬታማ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።

የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ለስራ ዕድል ፈጠራው ያለውን ጉልህ ሚና በማጤንም መንግሥት የግሉን ዘርፍ በማበረታታት ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ሁኔታዎችን ማመቻቸቱንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም በአመዛኙ በግብርና ላይ የተመሰረተ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንደነበር አስታውሰው፣ የብዝሃ ኢኮኖሚ አሰራርን በመከተል ከግብርና ባሻገር በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚ የሥራ ዕድል ፈጠራውን የሚያሳልጡ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብርም የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ ኢትዮጵያ ቁልፍ አጀንዳ ማድረጓን ገልጸው፣ ይህም የሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴው ላይ አበረታች ውጤቶች እንዲገኙ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ለአብነት ጠቅሰው፣ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በግንባታው መስክ የተገኘው ውጤት ተጠቃሽ መሆኑን አስረድተዋል።

በሀገሪቱ ወደ ሥራ የገቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review