በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለው የኢንቨስትመንትና የንግድ ትብብር በአዲስ ምዕራፍ መከፈቱ ተገለጸ

AMN- ህዳር 4/2017 ዓ.ም

የኢትዮ-ሩሲያ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

በመርኃ ግብሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታየ(ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን የንግድ ምክር ቤት ተወካዮች እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በዚሁ ወቅት፣ የኢትዮጵያና የሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ረዥም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገራቱ በተለይም በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ያላቸውን ትብብር እያጠናከሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የኢንቨስትመንትና የንግድ ትብብር በአዲስ ምዕራፍ መከፈቱን በአብነት አንስተዋል።

መንግስት ያደረገውን አጠቃላይ ሀገራዊ ሪፎርም ተከትሎ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች መምጣቷን ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ መታነጹን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ትብብር እየተሸጋገሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቴክኖሎጂ ሽግግር ይበልጥ ለማጠናከር መሰል መድረኮች ጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል።

የቢዝነስ ፎረሙ ዛሬና ነገ የሚካሄድ ሲሆን ሁለቱ ሀገራት በኢንቨስትመንትና በንግድ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ተገልጿል።

ከሳምንታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሩሲያ በተካሄደው 16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ መሳተፋቸው ይታወሳል፡፡

ከጉባኤው ጎን ለጎን በተካሄደው የሁለቱ ሀገራት የመሪዎች ውይይት የሀገራቱን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር ስምምነት ተደርጓል፡፡

የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎም እንዲህ ያሉ ፎረሞችና ተግባራዊ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review