በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም እየተተገበሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ውጤት እያሳዩ ነው-የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

You are currently viewing በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም እየተተገበሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ውጤት እያሳዩ ነው-የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

AMN – ጥር 16/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም እና የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ እየተተገበሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ውጤት እያሳዩ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በአጋር አካላት ድጋፍ የሚተገበሩ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በቢሾፍቱ ከተማ ገምግሟል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም እና የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርፃ ተግባራዊ እያደረገች ነው።

በዘርፉ የወጡ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በማስፈጸም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በቴክኒክ፣ በአቅም ግንባታ፣ ሀብት ማሰባሰብና በሌሎች ጉዳዮች በትብብር ማዕቀፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት ያላቸው 35 የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋሚያ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው አፈጻጸማቸውም ውጤታማ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ከአጋር አካላት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚመጣው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

መድረኩ ለፕሮጀክቶቹ ማስፈፀሚያ የወጣው ሀብት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን በመገምገም የተገኙ ውጤቶች፣ የገጠሙ ችግሮች መለየት እና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ በቀጣይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መደረግ የሚገባቸውን አቅጣጫዎች ተመላክተዋል።

ተሳታፊዎቹ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታም በአለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በመሀመድኑር አሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review