AMN – ጥር- 23/2017 ዓ.ም
የብልጽግና ፓርቲ “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ አጭር እና 60 ዓመት ያልሞላው ነው ብለዋል፡፡
ለውጥ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ለውጥን መምራት መቻል እንደሚያስፈልግ እውቀቱ ባለመኖሩ ምክንያት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ባለፉት ስልሳ አመታት አላስፈላጊ ውጣ ውረዶች ተስተውለዋል ብለዋል፡፡
አንድ ፓርቲ ለውጥን መምራት እስካልቻለ ድረስ የፓርቲ ህልውና እንደማይኖረውም ነው የገለጹት፡፡
ለውጥ መፍጠር ማለት ስላለው ችግር ፣ ድካም እና ውድቀት አብዝቶ መንቀፍ ብቻ ሳይሆን መፍትሔ ማመላከት እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ያለፉት የ60 ዓመታት የፖለቲካ ታሪካችንም በወቀሳና በነቀፋ የተሞላ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብልጽግና ሊያፈርስ የሚፈልገው በርካታ ኋላ ቀር አሠራሮችና ልምምዶች መኖራቸውን የተናገሩት የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፒያሳን ማፍረስ ብቻ ሳይሆን አልቆ መገንባት የብልጽግና መለያው ነው ሲሉ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
የአንድ ፓርቲ አስኳሉ ሀሳብ መሆኑን ያነሱ ሲሆን ሀሳብ የሌለው ፓርቲ ለውጥ ቢያመጣ እንኳን ለውጡን ለመምራት ይቸገራል ብለዋል፡፡
አክለውም ብልጽግና ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር በቀል እሳቤ ነድፎ የመጣ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ብልጽግና መደመር ለኢትዮጵያ ፍቱን መድሀኒት ነው ብሎ ይዞ ሲመጣ በሚያሳዝን መልኩ ባለፉት 6 ዓመታት አማራጭ ሀሳብ ይዞ የመጣ ግለሰብ፣ ቡድን እና ፓርቲ አላየንም” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በተቀዱ እሳቤዎች ያጋጠሙንን ችግሮች ስለምናውቅ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጭ ሀገር በቀል ሀሳብ ይዘው የሚመጡ ከሆነ ፓርቲያቸው ለመማር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሀሳብ የለሽ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች ለአጭር ጊዜ ድል የረዥም ጊዜ ሽንፈት ያመጡብናል ለዚህም ነው አማራጭ ሀገር በቀል ሀሳብ የሚያስፈልገው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፓርቲዎች ጉባኤ ታሪክ መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚካሄድ ጉባኤ የብልጽግና ጉባኤ ብቻ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በማሬ ቃጦ
All reactions:
4040