በወቅቱ ከኢንዱስትሪ አብዮት መስፋፋት ጋር ተያይዞ በበለጸጉ ሀገራት የሚገኙ ከተሞች በህዝብ ብዛት እየተጨናነቁና የንፅህና መጓደል እና ለኑሮም ምቹ አለመሆን ዋነኛ ችግራቸው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ከ1980ዎቹ ጀምሮ በበለጸጉትም ሆነ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ከተሞች የህዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ስለመምጣቱ የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል፡፡
የ‘How cities are changing’ መጣጥፍ ፀሐፊ ፕሮፌሰር ግሬግ ክላርክ እንደሚሉት እ.ኤ.አ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በህዝብ ብዛት መጨናነቅ የጀመሩና በጊዜ ብዛት የወየቡ ከተሞች ዕድሳት ባይደረግላቸው እጣፈንታቸው ሞት እንደነበረ ያስረዳሉ፡፡ ከተማን መልሶ የማልማት ፅንሰ-ሐሳብን ተግባራዊ ያደረጉት ከተሞች ለተሻለ የመኖሪያ አካባቢ እና ለምቹ የአኗኗር ዘይቤ እንዲሁም ዜጎች የተሻለ ኢኮኖሚ እንዲኖራቸው አስችለዋልም ባይ ናቸው ፕሮፌሰር ግሬግ፡፡
ፕሮፌሰሩ ከተማን በማደስ ጎዳናዎቻቸውን ያጸዱ፣ ለተሽከርካሪዎችና ለእግረኞች መደላድል የፈጠሩ፣ ያረጁ ከባቢዎችን ያደሱ ከተሞች የኢኮኖሚ መነቃቃት ስለማምጣታቸው የበርካታ ከተሞችን ተሞክሮ በመጠቃቀስ ማሳያ አድርገዋል፡፡ ስልታዊ በሆነ መልኩ በታቀደ የከተማ እድሳት እና እድገት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በመስራት ከተሞቻቸውን ወደ ህይወት ከመመለሳቸውም በላይ በስራ እድል ፈጠራ፣ ምቹ እና ክፍት መዝናኛ ስፍራችን በመፍጠር፣ የትራንስፖርት መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድም ስኬት አስመዝግበዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍም የተወሰኑትን ለአብነት እንቃኛለን፡፡
የስኮትላንድ ዋና ከተማ ኤድንብራህ በዓለም ላይ ካሉ ዕድሜ ጠገብ ከተሞች መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡ ኤድንብራህ ከተማ የተመሠረተችው ከ7ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ነው። ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የስኮትላንድ ዋና ከተማ በመሆን እያለገለች ትገኛለች። ዕድሜ የተጫጫናት ከተማዋ በአንድ ወቅት ለመልሶ መሰራት የቀረበ ከባድ ለውጥ አስፈልጓት እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ኤድንብራህ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ባሉት 25 ዓመታት ውስጥ በርካታ ዋና ዋና የማደስ ፕሮጀክቶችን በመሃል ከተማ አካሂዳለች። በአንድ ወቅት አይነኬ ይመስሉ የነበሩት በልዑል ስም ተሰይመው የነበሩ ጎዳናዎች ሳይቀር ሙሉ በሙሉ መፍረስ እና መልሶ ግንባታን ያካተቱ ሥር ነቀል እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል። ይህም ከተማዋን ከሞት ወደ ህይወት እንዳመጣት ፕሮፌሰሩ በመጣጥፋቸው አስፍረዋል፡፡
በመልሶ ግንባታው ምክንያት ኤድንብራህ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከልን ጨምሮ ዋና ዋና የፋይናንስ ኩባንያዎችን ስባለች፤ መቀመጫቸውንም በእርሷ እንዲያደርጉ አስገድዳለች፤ ከተማዋ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ገጽታዋን በመቀየሯ በግሬት ብርቴን አካባቢ ከለንደን ቀጥሎ የቱሪዝም መዳረሻ መሆን በመቻሏ ጠንካራ የከተማ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንደረዳት መረጃው ያመላክታል፡፡
የከተማዋ የድሮ እና የአሁን ገፅታ እ.ኤ.አ በ1999 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
ከተማዋ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ቀርፃ ችግኝ በመትከል አረንጓዴያማ እና ንፁህ፣ ለነዋሪዎቹም ሆነ ለጎብኚዎች የተስማማች፣ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን ዜሮ ለማድረግ እየሠራች ያለች ከመባል አልፋ የዓመቱ የዓለማችን አስተማማኝ የቱሪስቶች ማዳረሻ ተብላም ተሸልማ እንደነበር በፕሮፌሰሩ መጣጥፍ ተጠቅሷል፡፡
ኤድንብራህ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ በዓለም የምትታወቅበትን ሰፋፊ የአረንጓዴ መናፈሻ ስፍራዎችን በመጠበቅ አስተማሪ ሥራዎችን በመሥራት፣ ዘመናዊ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት በመዘርጋት፣ ለእግረኞችም ሆነ ለብስክሌተኞች አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በመገንባት ተጠቃሽ ከተማ ናት። ይህም በዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ዘንድ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን አድርጓታል።
ከተማዋ በዓለም በምሳሌነት የሚጠቀሱ አረንጓዴ የለበሱ 112 ፓርኮችን መገንባት እና ንፁህ አካባቢ መፍጠር ችላለች። ከተማዋ ዋና የቱሪዝም ማዕከል ስትሆን በየዓመቱ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይጎበኟታል። ይህም ለኢኮኖሚዋ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ገቢ ያስገኝላታል። በከተማዋ ከተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ነፃ የሆኑ እና ለብስክሌት ተጠቃሚዎች ብቻ የሚያገለግሉ 70 ኪሎ ሜትር መስመሮችን ዘርግታለች።
በእግር ለመጓዝ ምቹ የሆነችው እና በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማት ያሸነፈችው ኤድንብራህ የአስደማሚ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎችን በመገንባት ትልልቅ የቴክኖሎጂ አፍላቂ ኩባንያዎችን ያፈራች እንዲሁም የባህል እና የጥበብ ማዕከላት መገኛ በመሆኗ በቱሪስቶች ተመራጭ ለመሆን የበቃች ከተማ እንደሆነች ተመስክሮላታል፡፡
ኤድንብራህ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም በቅርስነት የተመዘገበች፤ የዓለም ረጅሙን የአርት ፌስቲቫል የምታዘጋጅ፤ የአውሮፓ ትልቋ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል፤ አራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ስመጥር ዩኒቨርስቲዎች መገኛ፤ የታሪካዊ ቅርሶች ማዕከል፤ የሳይንስ እና ምርምር ማዕከል፤ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም መሠረት ልማት ያሟላች ስትሆን ለሌሎች ከተሞችም በጥሩ ምሳሌነት ተጠቀሳለች። ይህ ሁሉ ውጤት የተገኘው ከተማዋ ባከናወነችው የኮሪደር ልማት ስራ አማካኝነት ነው፡፡

ላቲን አሜሪካዊቷ ሀገር ብራዚል ከተሞችን መልሶ ማልማት ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በሪዮ ዲ ጄኔሮ ባካሄደችው የኮሪደር ልማት ስራ አረጋግጣለች፡፡ ሪዮ ዲ ጄኔሮ እ.ኤ.አ በ1565 በፖርቹጋሎች እንደተመሰረተች መረጃዎች ያትታሉ። ስፋቷ 1 ሺህ 221 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሆነው ሪዮ ዲ ጄኔሮ፣ ከ26ቱ የብራዚል ግዛቶች አንዷ የሆነችው የሪዮ ዲ ጄኔሮ ግዛት ዋና ከተማ ናት። 200 ዓመታት ለሚሆን ጊዜም የብራዚል ዋና ከተማ ሆና ቆይታለች።
ሪዮ ከዓመታት በፊት ባካሄደችው የወንዝ ዳርቻ ልማትም በርካታ ትሩፋቶችን ተቋድሳለች፡፡ በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል የሚገኘው ፖርቶ ማራቪልሃ የተሰኘ የውሃ አካል የተገኘው ከተማዋ ባካሄደችው በዚሁ የመልሶ ግንባታ ሥራ ነው፡፡ 5 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታን የሚሸፍነው ይህ የውኃ ዳርቻ የቱሪስቶችን ቀልብ ከሚስቡ የከተማዋ ክፍሎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማ ከተማዋን መልሶ በማልማት ውበቷን በማሳደግ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ነው፤ ተሳክቷልም፡፡
የከተማ ዕድሳቱ የውሃ አቅርቦት፣ የመፀዳጃ ቤት ሽፋን፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን ማዘመን፣ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታን እውን ለማድረግ፣ የጋዝ እና የቴሌኮም መሠረተ ልማትን ማሟላት አስችሏል፤ ፕሮጀክቱ 5 ኪሎ ሜትር ዋሻዎች፣ 70 ኪሎ ሜትር መንገዶች፣ 650 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገዶች፣ 17 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ እና 15 ሺህ ዛፎች እንዲሁም የከተማ ንፅህና መጠበቂያ እና የሕክምና ተቋማትን አካትቷል።
ሪዮ ዲ ጄኔሮ አስደማሚ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ የባህል፣ የጥበብ አውድማ፣ የታሪክ እና የእውቀት እምብርት የሆነች በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ቀዳሚ የቱሪስቶች መዳረሻ ከተማ ናት። ሪዮ የምድራችን ትልቁን የካርኒቫል በዓል በማዘጋጀት እና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን በመሳብ ትታወቃለች። በየዓመቱ የሚዘጋጀው የሪዮ ካርኒቫል የምድራችን ትልቁ ትዕይንት ለመባል በቅቷል። ካርኒቫሉ የሚዘጋጅበት ስፍራ በኮሪደር ልማት ከተገኙ ሀብቶች መካከል ነው፡፡
ከተማዋ ባላት የተፈጥሮ ገጸ በረከቶች፣ የከርኒቫል ኩነቶች፣ የሳምባ ዳንስ፣ ቦሳኖቫ ባህላዊ ትዕይንቶች፣ የወንዝ ዳርቻ መዝናኛዎች፣ ተራራዎች፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐውልት፣ ሆቴሎች፣ በተራራዎች የተሠራው የሽቦ ላይ መኪና መዝናኛ የሚገኙባት በመሆኑ በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ በቱሪስቶች በቀዳሚነት እንድትጎበኝ አድርገዋታል። ዝነኛው የኮፓካባና የወንዝ ዳር መዝናኛን ጨምሮ 373 የወንዝ ዳርቻ መዝናኛዎች ለከተማዋ የቱሪዝም ዘርፍ የጀርባ አጥንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
የከተማዋ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂ.ዲ.ፒ) 201 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፣ በሀገሪቱ በትልቅነቱ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዕድሜ ጠገብ ዛፎችን የያዘው የእፅዋት ማዕከል ለከተማዋ ተጨማሪ የቱሪዝም መስህብ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
ብራዚላውያኑ ዕድሜ ጠገቧን ሪዮ ዲ ጄኔሮን በምን መልኩ ስላደሷት ከልማቱ መቋደስ ቻሉ? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ ውድሮ ዊልሰን ዓለም አቀፍ ምርምር ማዕከል እ.ኤ.አ በ2014 ያወጣ መረጃ ምላሽ አለው፡፡ ማዕከሉ እንደሚለው በአንድ በኩል ከተማዋ ያሏትን ወንዞች አፅድታ መጠቀም መቻሏ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዕድሜ ጠገብ መንደሮቿን መልሳ ማልማት በመቻሏ ነው፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ