AMN- የካቲት 15/2017 ዓ.ም
በከተሞች በየዘርፉ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) ገለጹ።
በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ኮንፍረንስ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት በአዳዲስ እሳቤዎች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፎች ባከናወናቸው ተግባራት ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በተለይ በከተሞች በልማትና መልካም አስተዳደር መሠረታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ በየዘርፉ የመጣውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
መድረኩ በሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ላይ በተወሰኑ ውሳኔዎችና በተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ተግባቦትን ፈጥሮ ለተግባራዊነቱ በቅንጅት ለመትጋት ያለመ መሆኑንም አመልክተዋል።
በከተሞች እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት የከተሞችን ገፅታ እየቀየረ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) ናቸው።
በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት እየተተገበሩ የሚገኙ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች በከተሞች የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየፈታ ነው ብለዋል።
ከተሞችን ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የህብረተሰቡ የልማት ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች፣ የባህልና የሀይማኖት አባቶች የተገኙ ሲሆን በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ላይ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
በመድረኩ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረ እግዚአብሔር እንዲሁም የክልል፣ የዞንና የከተማ ሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።