በኮሪደር መሠረተ-ልማት ላይ በእግረኞች መንገድ በተሽከርካሪ በመሄድ ደንብ ተላልፈው የተሰወሩ አሽከርካሪዎች 300 ሺህ ብር መቅጣታቸዉን የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ እንዳስታወቁት አሽከርካሪዎቹ በትላንትናው እለት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ወሎ ሰፈር አካባቢ በተሠራው የኮሪደር ልማት መሰረተ ልማት የእግረኞች መንገድ ላይ በተሽከርካሪ በመሄድ ደንብ መተላለፋቸዉን ተናግረዋል፡፡

አሽከርካሪዎቹ የደንብ ጥሰቱን ፈጽመዉ የተሰወሩ ቢሆንም ከአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ፖሊሶች ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር በማዋል መቀጣታቸዉን ገልጸዋል፡፡
ግለሰቦቹ በህብረተሰቡ ጥቆማ መሠረት ክትትል በማድረግ 3 አሽከርካሪዎች ከነ ተሽከርካሪአቸው በቁጥጥር ስር በማዋል እያንዳንዳቸው 100.000 (አንድ መቶ ሺህ ብር )በድምሩ 300,000/ሦስት መቶ ሺህ/ ብር መቀጣታቸዉን ገልጸዋል ።

ባለስልጣኑ የህብረተሰቡ የጋራ ሀብት የሆኑ የኮርደር ልማትና በሌሎች አካባቢ የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን፣ ለህዝብ የተሰሩ አረንጓዴ ስፍራዎች እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችን ደህንነት በመጠበቅ በሀላፊነት እንዲገለገል የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ