የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ23ኛ የፊፋ ዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ስድስተኛ ጨዋታውን ዛሬ ከጅቡቲ ጋር ያደርጋል።
የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ በሞሮኮ ኤል ጄዲካ ከተማ በሚገኘው ኤል አብዲ ስታዲየም ይካሄዳል።
ዋልያዎቹ ከቀናት በፊት ከግብጽ ጋር ባደረጉት አምስተኛ የምድብ ጨዋታ 2 ለ 0 ተሸንፈዋል። በምድብ አንድ ሶስት ነጥብ ይዘው አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ጅቡቲ ቡርኪናፋሶ ጋር ባደረገችው የማጣሪያ መርሃ ግብር የ4 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዳለች። ቡድኑ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታው የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ማድረጉን ኢዜአ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ እ.አ.አ በ2026 በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት ይሳተፋሉ።
በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ 54 የአፍሪካ ሀገራት በዘጠኝ ምድብ ተከፍለው የማጣሪያ ጨዋታ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
አፍሪካ በዓለም ዋንጫው 9 ሀገራት በቀጥታ ታሳትፋለች። ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው የ5 ሀገራት ተሳትፎ እድገት አሳይቷል።
አንድ የአፍሪካ ቡድን በሌሎች አህጉራት ከሚገኙ ሀገራት ጋር በሚደረግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ካሸነፈ አህጉሪቷን የሚወክል 10ኛ ሀገር ይሆናል።