በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ተባለ

You are currently viewing በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ተባለ

የትንሳኤ በዓልን ስናከብር በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመተጋገዝ እና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ሲሉ የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡

የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ የኃይማኖት አባቶቹ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፣ በዓለ ትንሳኤ የእግዚአብሔር ፍቅር መገለጫ እና ተስፋችን ማሳያ መሆኑን በመገንዘብ ለእግዚአብሔር ክብር እና ለሰው ልጆች ደኅንነት በአንድነት በመቆም ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታረዙት፣ ለታመሙትና ለታሰሩትም ሁሉ ካለን ከፍለን በመስጠት ከእኛ ጋር በመንፈስና በሞራል በዓሉን እንዲያሳልፉ እናድርግ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፣ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ዋና ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የትንሳኤ በዓልን ስናከብር በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመተጋገዝ እና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ለተቸገሩ ወገኖችም ካለን በማልበስና በማብላት አለንላችሁ እንድንላቸው ይገባል ሲሉ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመልዕክታቸው፣ በዓለ ትንሳኤ የእግዚአብሔር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል ብለዋል።

“ደግ መስራትና ክፉን መጠየፍ የፈጣሪ የማይለወጥ ጠባይ ስለሆነ ምዕመናንም ይህን ሊወርሱ ይገባል” ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ኃይማኖታዊው አስተምህሮም የሚያሳየን ይህንኑ ነው በማለት በዚህ መርሕ መሠረት በሥራ በመትጋትና በፍጹም ፍቅር በመኖር ሕይወታችንን ይበልጥ ልናሳድገው ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡

ጌታችን የመልካም ነገር ሁሉ አርአያና መሪ እንደመሆኑ መጠን አዲሱን መንገድ ከፍቶ እንድንጓዝ አድርጎናል። በመሆኑም ፈጣሪ ባሳየን የህይወት መንገድ ልንመራ ይገባል ብለዋል፡፡

ዘር ሳይኖር ፍሬ እንደማይገኝ ሁሉ ኃይማኖታዊ ትንሳኤም ያለ ኃይማኖትና ስነ ምግባር ሊገኝ አይችልም፡፡ ጌታችንም ይህን ሲያስተምር መልካም ያደረጉ ለህይወት ትንሳኤ ይነሳሉ፤ ክፉ ያደረጉም ለፍርድ ትንሳኤ ይነሳሉ ሲልም ኃይማኖታዊ አስተምህሮቱን አስረድተዋል፡፡

ስለ ሀገሪቱ ሰላም ሁኔታ ሲያብራሩም ታጥቃቹ በትግል ላይ የምትገኙ አካላት ሰላም ስለቸገረው ህዝብ ብላችሁ ለሰላምና ለውይይት ዕድል ስጡ ሲሉም ተማፅነዋል፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ጥሪ ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ሰዎች ከመልካም ስነ ምግባር በራቁ ቁጥር ህይወት መራራ እንድትሆን ትገደዳለች፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ በስነ ምግባር እየተመራን በደልን በይቅርታ እየዘጋን፣ እስከ ዳርቻ በመዝለቅ በእርቅ ደምን እያደረቅን በወንድማማችነት ፍቅር ተስማምተን በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት ኖረናል፡፡

በመሆኑም በእርቅ በይቅረታና በውይይት የማይፈታ ችግር የለምና መጨካከን እንደመፍትሄ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ለመላው ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልዕክት ችግራችን ራሳችን ሸምጋይና ተሸምጋይ ሆነን ችግሮቻችንን ለመፍታት በብርቱ ልንሰራ ይገባል። ሰለማዊ መንገድ በመከተልም ለኢትዮጵያ አንድነትና ዕድገት አጥብቃችሁ ጥረት አድርጉም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ በበኩላቸው፣ የትንሳኤ በዓል የክርስቲያን ሕይወት መሠረትና ምሰሶ መሆኑን አስታውሰው፣ ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤን በዓል ሲያከብር የተቸገሩትንና ያጡትን በማሰብ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሰዎች ዕለታዊ ሕይወት ውስጥ ብዙ የሚያስጨንቁና የሚያሳዝኑ ነገሮች ያጋጥማሉ ያሉት ካርዲናሉ፣ ህዝበ ክርስቲያኑም በዓሉን ሲያከብር በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ የተራቡና የተጠሙትን በማሰብ ብሎም ካላቸው ላይ በማካፈል በጋራ እንዲያከብሩም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የሰው ጥበብ እስከተወሰነ ድረስ ያደርስ ይሆናል ነገር ግን ጌታችንን በመከተል ብቻ የሚገኙ ብዙ በረከቶች አሉ ብለው፣ የእርሱ ተከታይ የሆኑ ክርስቲያኖችም በሰዎች መካከል መከፋፈል፣ መድሎ፣ ምቀኝነትና ጭካኔን ሳይፈጥሩ በትህትናና በመረዳዳት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

በመስቀልና በትንሳኤው የተሰበረው ይጠገናል፤ የደከመው ይበረታል፤ የወደቀው ይነሣል፤የተሸነፈው ያሸንፋል፤ ይህንንም ለማክበር በትንሳኤው እንሰባሰባለን ያሉት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ፣ ይህንንም ለበጎ ዓላማና ተግባር ማዋል ይገባል ብለዋል፡፡

አክለውም በትንሳኤ በዓል መላው ምዕመናን ልናደርገው የሚገባን የተቸገሩትን ወገኖች በመርዳትና በመተሳሰብ፣ ያዘኑትን በማጽናናትና በማሰብ እንድታከብሩና ደስታቸውንም ፍፁም እንድታደርጉ ፀጋችሁንም እንድታበዙ አደራ ማለት እወዳለሁ የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ዋና ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ የትንሳኤ በዓልን ስናከብር እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅርና ከዚህም የተነሳ አንድያ ልጁን ስለእኛ ሐጥያት ለመስቀል አሳልፎ መስጠቱን እንድናስብ ግድ ይለናል ብለዋል፡፡

ይህም ከዘላለም ሞት ወደ ዘላለም ህይወት መሸጋገራችንን፤ ከሐጢያት ባርነት ነጻ መውጣታችንን በመገንዘብ እግዚአብሔርን ይበልጥ እንድናመሰግነው እና እለት ከእለትም በቅድስና እንድናመልከው ሊያደርገን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ኃጢያታችንን ስለዋጀን የመንግስቱ ወራሽ በመሆን በጽኑ ተስፋ ተደላድለን እንድንቆም ስለአደረገን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ብቻ ይሁን ሲሉ አክለዋል፡፡

ቄስ ደረጀ ጀንበሩ ትንሳኤ ጥላቻ ፍቅር፣ መለያየት በአንድነት፣ ሐዘን በደስታ የተቀየረበትን እና የእግዚአብሔር ድንቅ ፍቅር የተገለጠበት ስለሆነ ከሁሉ በፊት በእኛ በክርስቲያኖች መካከል እውነተኛ ፍቅር መታየት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ትንሳኤ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተራራቁ የሚቀራረቡበት በዓል ነውና በያለንበት ታርቀን በማስታረቅ መልካም ምሳሌነታችን ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ  ያስፈልጋል። ይህ ከሁሉ ምዕመናን የሚጠበቅ መለኮታዊ ትዕዛዝ ስለሆነ ቸል የምንለው ጉዳይ አይሆንም በማለት ተናግረዋል፡፡

እንደ ቄስ ደረጀ ገለጻ፣ ማንም ባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ፡፡  ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅር ልበሱት ብለዋል።

እግዚአብሔር እኛን ከኃጢያት እና ከዘላለም ሞት ለማዳን ልጁን የላከው ለሰው ልጆች ካለው ታላቅ ፍቅር የተነሳ በእኛም መካከል መንገስ ያለበት ያ መለኮታዊ ፍቅር እንደሆነ ገልጸዋል። ፍቅር ከራሳችን ይልቅ ሌላውን እንድናስቀድም ስለሚያደርግ ከራሳችን አልፈን ለሀገራችን ሰላም እና ለህዝባችን አንድነት በቅንነት እና በትጋት ለመስራት ፍቅር አቅም ይሆነናል፡፡ በእለት ከዕለት ኑሯችንም ሆነ ተግባራችን በቅድስና እንመላለለስ ብለዋል፡፡

በፍጹም ቅንነት መከባበርና መደማመጥ፣ በእርቅ የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እና የህዝባችንን አንድነት በጽኑ አለት ላይ ለማቆም መወያየት ግድ እንደሚል ተናግረዋል፡፡ በየቤታችን የትንሳኤን መታሰቢያ እለት ስናከብር ከተቸገሩ ወገኖቻችን ጋር ያለንን በማካፈል እና የክርስቶስን ፍቅር በማሳየት እንዲሆንም ቄስ ደረጀ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶ እንዳስታወቁት ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርም ሆነ የይቅርታ መንፈስን ለሁላችንም ያካፈለን በመሆኑ ምክንያት እኛም ከድርጊቱ መማር እና መተግበር ይገባናል ብለዋል፡፡

የትንሳኤውን በዓል በምናከብርበት ጊዜ በተለይ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተጓዘበትን የትህትና እና የስቃይ መንገድ እንደሚያስታውሰን ገልጸው፣ እኛም በፍቅር በመተሳሰብ፣ በትህትና ማክበር እንደሚገባን ተናግረዋል፡፡

እንደ ፓስተር ጻድቁ ገለጻ ክፋት፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት፣ መጥፎ ነገሮች ሁሉ በትንሳኤው ብርሃን ስለተሻሩ እኛም በህይወታችን ውስጥ ያሉትን መጥፎ ነገሮች በማስወገድ በግል ህይወታችን፣ በማህበረሰብ፣ እንደ ሀገርም የትንሳኤውን ኃይል በመተግበር የይቅርታ፣ የምህረትና የእርቅን መንፈስ በመካከላችን እንድናሰፍን አሳስበዋል፡፡

በጋዜጣዋ አዘጋጆች

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review