በመዲናችን አዲስ አበባ ዛሬ እና ነገን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይካሄዳሉ። ከሰሞኑም በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ኩነቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች የተሰናዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የቴአትር መርሃ ግብር፣ የስዕል አውደ ርዕይ እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መርሃ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
ሥዕል
የሰዓሊ ሄኖክ ፀጋዬ “በመንገዴ ላይ” የሥዕል አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ረዕቡ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ቦሌ በሚገኘው እንጦጦ ጋለሪ በይፋ የተከፈተው ይህ አውደ ርዕይ፣ ሰዓሊው ተፈጥሮ እና ታሪክን መነሻ በማድረግ የሰራቸው የጥበብ አሻራዎችን ለዕይታ ያበቃበት ነው ተብሏል፡፡ ሰዓሊው የሥነ ጥበብ አፍቃሪያንም መጥተው አውደ ርዕዩን እንዲመለከቱ ጋብዟል፡፡ ይህ አውደ ርዕይ እስከ መጪው ሚያዝያ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡
በሌላ መረጃ ሰባት ወጣት ሰዓሊያን በጋራ ያዘጋጁት “ሪትም” የስዕል ዓውደ-ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ ከሳምንት በፊት በይፋ በተከፈተው በዚህ የሥዕል አውደ-ርዕይ ላይ ከተሳተፉት ወጣት ሰዓሊያን መካከል አለምሰገድ በሃይሉ፣ አሌክሳንደር ፍስሃዬ፣ ዳዊት ጎሳዬ፣ ማህሌት አፈወርቅ፣ ሳሙኤል እንዳለማው ይገኙበታል፡፡ መልከ-ብዙ ግለሰባዊና ማህበረሰባዊ ጭብጦችን የሚዳስሱ ስራዎች የቀረቡበት ዓውደ-ርዕይ ነው። የሥዕል ዓውደ-ርዕዩ እየታየ ያለው በላፍቶ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ጋለሪ ውስጥ ሲሆን፣ የሥዕል ዓውደ-ርዕዩን እስከ መጋቢት 23 ቀን ድረስ ለተመልካቾች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡
ሙዚቃ
“ጌዲ በተራ” ቅፅል ስሙ የሚታወቀው የጌድዮን ዳንኤል የሙዚቃ አልበም ለአድማጭ ደረሰ፡፡ “የኛ ሰው” የሚል መጠሪያ የተሰጠው አዲሱ አልበሙ ትናንት አርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም ነው ለአድማጭ የደረሰው። በናሆም ሪከርድስ የዩቱብ ቻናልና በሌሎችም አማራጮች አድማጮች ያገኙታል ተብሏል፡፡ ከዘጠናዎቹ ተወዳጅ ድምፃውያን መካከል አንዱ የሆነው ጌዲዮን ዳንኤል (ጌዲ በተራ) ከዚህ ቀደም ለአድማጭ ካቀረባቸዉ ሦስት የሙዚቃ አልበሞች በተጨማሪ በርካታ ነጠላ ዜማዎችን ለሙዚቃ አድማጮች አድርሷል፡፡
ሙዚቃን በተመለከተ ሌላኛው መረጃ እውቋ ሙዚቀኛ ኩኩ ሰብስቤ በቅርቡ የሙዚቃ አልበሟን ለሙዚቃ አድማጮች እንደምታደርስ አሳውቃለች። ኩኩ በማህበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጿ፣ “ሰላም በመላው ዓለም የምትገኙ ወዳጆቼ እንዲሁም አድናቂዎቼ ‘ደጃዝማች’ የተሰኘውን አዲሱ የሙዚቃ አልበሜን በቅርብ ቀን በራሴ የዩቱብ ቻናል እና በሁሉም የዲጂታል መተግበሪያዎች ወደ እናንተ አደርሳለሁ” ስትል አሳውቃለች። የሙዚቃ አልበሙ ከመጪው ፋሲካ ቀደም ብሎ እንደሚለቀቅ ይጠበቃል፡፡
መጻሕፍት
ከዚህ ቀደም ገበያ ላይ የጠፉትን ጨምሮ አዳዲስ መጻሕፍት ለንባብ ማብቃቱን የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ አስታወቀ፡፡ ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል የዕውቅ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ግለ ታሪክ፣ የጉዞ ማስታወሻ፣ የኢትዮጵያን ሥነ ጥበብ፣ ታሪክና ሳይንሳዊ እሳቤዎችን የያዙ መጻሕፍት ይገኙበታል ተብሏል፡፡
አካዳሚ ፕሬሱ መልሶ ለገበያ ካቀረባቸው መጻሕፍት መካከል፣ በልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም የተጻፈው “የትውልድ አደራ”፣ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአውሮጳና መካከለኛው ምሥራቅ 1903 የተሰኘው፣ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ተጽፎ በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የተሰናዳው መጽሐፍ፣ ‘ከደስታ ባለፈ፤ ተፈጥሯዊ የሩካቤ ሂደትና ውጤቱ’ በሚል ርዕስ በማንይንገረው ሸንቁጥ የተጻፈው መጽሐፍ፣ የተውኔት ዝግጅት መሠረታውያን የተሰኘው በተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) የተሰናዳውና እንዲሁም ‘Ethiopia Illustrated፡ Church Paintings, Maps and Drawings’ By Dorothea Mcewan በሚል ርዕስ በዶሮቲአን ማኪዋን የተጻፈው መጽሐፍ ይገኙበታል፡፡ መጻሕፎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጻሕፍት ማዕከል ጨምሮ በተለያዩ መጻሕፍት መሸጫ መደብሮች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ኪነ ጥበባዊ የውይይት መርሃ-ግብር
ሁለገቡ የኪነ ጥበብ ባለሙያ አርቲስት ቢኒያም ወርቁን የሚያመሰግን ዝግጅት ሊካሄድ ነው፡፡ የፊታችን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ከ11 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ የምስጋና እና የአክብሮት ፕሮግራሙ ይከናወናል። በዝግጅቱ ቢኒያም ያስተማራቸው ታዋቂ አርቲስቶች ይገኛሉ ተብሏል፡፡ የአርቲስት ቢኒያም ተማሪዎች ከሆኑት መካከል ሰለሞን ቦጋለ፣ ፍቃዱ ከበደ፣ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ)ን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎቹ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ አርቲስት ቢኒያም ወርቁ ከ20 በላይ ፊልሞች እና ከ7 በላይ ቴያትሮችን በደራሲነት፣ በአዘጋጅነት፣ በተዋናይነት እና በዳይሬክተርነት ሰርቷል፡፡
የቴአትር መርሃ ግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ባሎች እና ሚስቶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:00 ሰዓት ባቡሩ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ 11፡30 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ይታያል። እሁድ በ8፡00 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን እምዬ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ይታያል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት ሐሙስ ደግሞ 11:30 ሰዓት ጎዶ’ን ጥበቃ በብሔራዊ ቴአትር፣ አርብ በ12፡00 ሰዓት ዋዋጎ በዓለም ሲኒማ፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡
በአብርሃም ገብሬ