
AMN – ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ የባለድርሻ አካላትና የህብረተሰብ ክፍሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ መጀመሩን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
በክልሉ የተጀመረው የባለድርሻ አካላትና የህብረተሰብ ክፍሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይም ተጠቁሟል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘገዬ አስፋው፣ ”ሁላችንም እዚህ የተሰበሰብነው ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ነው” ብለዋል።
ምክክር የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ሁሉንም ባካተተ መልኩ ምክክር እንዲካሄድ ኮሚሽኑ በርካታ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ያለምንም ገደብ በመደማመጥና በመከባበር ሀሳባቸውን እንዲገልፁ ያሳሰቡት ኮሚሽነሩ፣ በዚህ ሁኔታ ከተወያየን የማንሻገረው ችግር የለም ብለዋል።
ሌላው ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በበኩላቸው፣ ችግሮችን ሁሉንም ባሳተፈ ምክክር መፍታት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን አስታውሰዋል።
ኮሚሽኑ ከጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አጀንዳ እያሰባበሰ መሆኑን ጠቁመው፣ በዛሬው እለትም የዚሁ አንዱ አካል የሆነው የባለድርሻ አካላት መድረክ መጀመሩን ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በጥልቀት በመወያየት ጠቃሚ አጀንዳዎችን ለይተው ለኮሚሽኑ እንዲያስረክቡም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።