‘ጣናነሽ 2’ አዳማ ስትገባ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች፣ የአዳማ ከተማ ከንቲባና የከተማው ነዋሪዎች አቀባበል አድርገውላታል።
ከጂቡቲ ዶላሬ ወደብ ተነስታ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ላይ የምትገኘው ‘ጣናነሽ 2’ ከረጅም ጉዞ በኋላ በዛሬው ዕለት ደግሞ አዳማ ከተማ ገብታለች።
‘ጣና ነሽ 2’ 150 ሜትሪክ ቶን ክብደት ሲኖራት ርዝመቷም 38 ሜትር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ከ188 ሰው የመጫን አቅም እንዳላትም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ በተለያዩ ሐይቆች ላይ በዘመናዊ ጀልባዎች የታገዘ የውኃ ላይ ትራንስፖርት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
ለዚህም የሚያግዙ ዘመናዊ ጀልባዎችን በማስመጣት በሀገር ውስጥ ሐይቆች ላይ ትራንስፖርትን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‘ጣና ነሽ 2’ ለዚሁ አገልግሎት ወደ መዳረሻዋ ባህር ዳር እየተጓጓዘች መሆኑን ተቋሙ አመልክቷል።
ወደፊትም ላንጋኖ እና ሻላን ጨምሮ በሁሉም ሐይቆች ላይ በዘመናዊ ጀልባዎች የታገዘ የውኃ ላይ ትራንስፖርት ለመስጠት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።
የ’ጣና ነሽ 2′ ጉዞ የተሳለጠ እንዲሆን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የየክልሎቹ የትራፊክ ፖሊስ አባላት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጀልባዋን ለማሳለፍ በመንገድ ላይ ያሉ የኤሌክትሪክ ገመዶችን በማንሳት እንዲሁም የሚቋረጡ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን በፍጥነት በመመለስ ርብርብ እያደረጉ መሆኑም ተመልክቷል።