“ባህላዊ መድኃኒት ቀማሚ ነኝ ፀሎት አደርግልሻለው ብርሽንም አበዛልሻለው” በማለት ከአንዲት ግለሰብ ከ736ሺ ብር በላይ ያታለለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

You are currently viewing “ባህላዊ መድኃኒት ቀማሚ ነኝ ፀሎት አደርግልሻለው ብርሽንም አበዛልሻለው” በማለት ከአንዲት ግለሰብ ከ736ሺ ብር በላይ ያታለለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

AMN- የካቲት 16/2017 ዓ.ም

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ጎፋ ቅዱስ ገብርኤል አደባባይ አካባቢ ነው። ተጠርጣሪው “የባህላዊ መድኃኒት ቀማሚ እና ፈዋሽ ነኝ በሚል” ‘አባ መንግስቱ’ የሚል ማህበራዊ ሚዲያ በመክፈት አንዲት ታዋቂ የኢትዮጵያ አርቲስት የሰጠችውን ኃይማኖታዊ የፈውስ ምስክርነት ከሌላ ሰው ላይ አውርዶ በራሱ አካውንት የፈወስኳት እኔ ነኝ በማለት ይለቃል።

ይህን ቪዲዮ የተመለከተች የግል ተበዳይ ‘ባህላዊ መድኃኒት እፈልጋለሁ’ በማለት ወደ ግለሰቡ በመደወል ስትጠይቅ እንደሚሰራላት ይነግራታል።

ከጊዜ በኋላ ግለሰቡ ‘አካውንትሽ ላይ ስንት ብር አለ’ ብሎ ግለሰቧን በመጠየቅ ‘ብርሽን አበዛልሻለው’ ብሎ በማሳመን በተለየ ስም በከፈተው የባንክ አካውንት በተለያዩ ጊዜያት እና ቀናት በድምሩ 652 ሺ ብር ወደ ራሱ አካውንት እንድታስገባለት ያደርጋል። ይህም አልበቃው ብሎ ከሌሎች ተበድራ 84 ሺ 800 ብር ተጨማሪ እንድታስገባለት ማድረጉን በጎፋ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የተጣራው የወንጀል ምርመራ መዝገብ ያስረዳል።

ተከሳሽ በአጠቃላይ 736 ሺ 800ብር እንዲላክለት ያደረገ ሲሆን ‘ብርሽ በዝቶልሽ ይመለስልሻል’ እያለ ቀጠሮ እየሰጠ ሲጠፋ እና መታለሏ የገባት የግል ተበዳይ ወደ ፖሊስ በመምጣት የተፈፀመባትን ወንጀል ትናገራለች። ፖሊስም የግለሰቧን አቤቱታ መነሻ በማድረግ እና የምርመራ መዝገብ በማደራጀት ለግለሰቡ የተላከበትን አካውንት ሲያጣራ ግለሰቧ በተለያዩ ቀናት በተለያየ አካውንት ገንዘቡን መላኳን አረጋግጧል።

ግለሰቡ በተለያዩ ስሞችና በተለያዩ ባንኮች አካውንት መኖሩን ያጣራው ፖሊስ ግለሰቡን የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ በማውጣት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ደቡብ ምዕራብ ክልል በምትገኘው ቴፒ ከተማ ድረስ በመሄድ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ግለሰቡ በቁጥጥር ከዋለ በኋላ በተላከለት ገንዘብ ኮድ (1) 05224 ደቡብ ምዕራብ ጊዜያዊ ሠሌዳ ያለው አንድ ባጃጅም የገዛ ሲሆን ተጠርጣሪው ከነ ኤግዚቢቱም በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።

አሁን አሁን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ‘እፈውሳለሁ ባህላዊ መድኃኒት ቀማሚ ነኝ’ የሚሉ ምንም አይነት እውቅናና ፍቃድ የሌላቸው ግለሰቦችን እያስተዋልን እንገኛለን ያለው ፖሊስ ህብረተሰቡ ውሳኔዎችን ከመወሰኑ በፊት ማንነታቸውን እና ትክክለኛነታቸውን በማረጋገጥ ለመሰል የወንጀል ድርጊቶች እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review