AMN – መጋቢት 5/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ወንዞችንና የወንዞች ዳርቻዎችን በሚበክሉ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡
ባለስልጣኑ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ወንዞችና የወንዞች ዳርቻ የበከሉ ድርጅቶችና ግለሰቦችን በዛሬው እለትም በደንብ ቁጥር 180/2017 መሰረት 3,176,000/ሶስት ሚሊየን አንድ መቶ ሰባ ስድስት ሺህ/ ብር የገንዘብ ቅጣት በመቅጣት አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
በዛሬው እለት ቅጣት የተወሰደውም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ 800,000 ብር፣ በልደታ ክፍለ ከተማ 750,000 ብር፣በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 426,000 ብር፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ 300,000 ብር፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 300,000 ብር በመቅጣት አስተዳደራዊ እርምጃ ወስዷል።

በተመሳሳይ በኮልፌ ክፍለ ከተማ 300,000 ብር፤ በአቃቂ ክፍለ ከተማ 300,000 ብር ቅጣት መቅጣቱንም አመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ በዛሬው እለት 7 ድርጅቶች እና 5 ግለሰቦችን በመቅጣት በድምሩ 3,176,000/ሶስት ሚሊየን አንድ መቶ ሰባ ስድስት ሺህ/ ብር በመቅጣት ለመንግስት ገቢ መደረጉን ተገልጿል።
ባለስልጣኑ፣ ወንዞችንና የወንዞች ዳርቻዎችን የሚበክሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ድርጊቱን በሚፈጽሙ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስታወቁን የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል፡፡