ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ማቋቋም ለምን አስፈለገ?

You are currently viewing ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ማቋቋም ለምን አስፈለገ?

የመንገድ መብራት ለከተሞች ዘርፈ ብዙ ትርጉም አለው፡፡ የከተሞች የስልጣኔ ምልክት ተደርገው ይወሰዳሉ። በማታና ሌሊት የሚደረገውን የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ በማድረግ፣ ወንጀልን በመከላከል፣ ከተሞችን ውበትና የተለየ ገፅታ በማላበስ ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካውያን መዲና እንዲሁም በዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ፣ ባለፉት ዓመታት ዘመናዊ የመንገድ መብራት በመገንባት የዘመነችና ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች ምቹ ከተማ እንድትሆን ለማስቻል በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፤ በመሰራት ላይም ይገኛሉ፡፡

በከተማዋ የመንገድ መብራት የመገንባትና የመጠገን ኃላፊነት በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ውስጥ በአንድ ክፍል ስር ተደራጅቶ ለ30 ዓመታት ሲመራ እንደቆየ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰብስብ ሁሴን ያነሳሉ፡፡

አዲስ አበባ እያሳየች ካለው ፈጣን እድገት አኳያ ለነዋሪዎቿ የምትስማማ፣ ዘመናዊ፣ ቀንና ሌሊት የሚሰራባት ከተማ እንድትሆን ለማስቻል የመንገድ መብራት የሚኖረውን ፋይዳ በመገንዘብና የረጅም ጊዜ ጥናት በማድረግ የመንገድ ዳር መብራት እራሱን ችሎ እንዲሰራ ለማስቻል የአዲስ አበባ የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለሥልጣን ተቋቁሟል። ባለስልጣኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 84/2016 መሰረት፤ በደንብ ቁጥር 166/2016 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ አምስት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሰብስብ እንደገልፁት፣ በከተማዋ በዋና ዋና መንገዶች አገልግሎት እንዲሰጡ የተገነቡ መብራቶች ለሚደርስባቸው ስርቆት እና ብልሽት በባለቤትነት ተከታትሎ ወደ አገልግሎት የሚመልስ አካል መፍጠርና ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ሌላኛው ተቋሙ እንዲቋቋም ምክንያት ሆኗል፡፡ 

የመንገድ መብራት ስራ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ስር በነበረበት ወቅት፣ ባለስልጣኑ መብራቶችን መትከል እና መጠገን ላይ ብቻ ነበር አተኩሮ የሚሰራው፡፡ ይህም የመንገድ መብራቶች ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መከታተልና ጉዳት ከደረሰ በኋላ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ላይ ችግር ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ተቋሙ ራሱን ችሎ ሲቋቋም 18 የሚሆኑ ተልዕኮዎችን ለመስራት አቅዶ ነው የተነሳው፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የመንገድ መብራት አንዱ ተልዕኮ ነው። በቀጣይም በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን የመብራት ፍጆታ ክፍያ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ነግረውናል፡፡

አቶ ሰብስብ እንደሚያብራሩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመብራት ሃይል አስተዳደር ባለሥልጣን የሚከውናቸው በርካታ ሥልጣንና ተግባራት እንደተሰጡት ያብራራሉ። እነዚህም ተቋሙን በቴክኖሎጂ የማዘመን፣ የሚሰሩ ዝርዝር ተግባራትን ለይቶ ማህበረሰቡ እንዲያውቃቸው አሰራርን የመዘርጋት፣ የመብራት መስመር ዝርጋታዎችን በተለይም ደግሞ በኮሪደር ልማቱ የሚዘረጉትን ሙሉ በሙሉ ከመሬት በታች እንዲሆኑ ማድረግ፣ ቀደም ሲል የነበረውን የመንገድም ይሁን የህንፃ መብራት የማቀናጀት እና ስታንዳርድ የማውጣት፣ ከዚህ በፊት ሲዘረጉ የነበሩትን ቀለማቸው የማይታወቁ እና ተገንብተውም ማህበረሰቡ ሳይገለገልባቸው የቆዩ የመንገድ መብራቶችን ሙሉ አቅምን ተጠቅሞ የመስራት፣ ነባር የመንገድ መብራቶችን የመጠገን፣ ወደ ስራ ያልገቡትን የማስገባት፣ አዳዲስ መስመሮችንም ማህበረሰቡን በሚመጥን መንገድ የመስራት ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል፡፡

የመንገድ ዳር መብራት መሠረተ ልማትን ጉዳት ሲደርስበት ጉዳቱን ያደረሰውን ሰው እንዲተካ የማድረግ፣ የመብራት መሰረተ ልማት ግብዓት አቅራቢዎች የብቃት ደረጃ መስፈርት የማውጣት እንዲሁም ተግባር ላይ መዋሉን የማረጋገጥ፣ በመንገድ መብራት መሰረተ ልማት ላይ ለሚሰቀሉ ስክሪኖች፣ ሲሲቲቪ ካሜራዎች፣ ዋይፋይ እና መሰል አገልግሎቶች ፍቃድ የመስጠት፣ የማደስ፣ የመሰረዝና ለመንገድ መብራት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያስፈልግ ለሚመለከተው አካል ጥያቄውን በማቅረብ እንዲቀርብለት ያደርጋል፡፡ እንዲሁም በመንገድ መብራት መሠረተ ልማት ላይ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን መከላከል፤ ተፈጽሞም ሲገኝ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ፣ በኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚነሱ ቅሬታዎች የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት፣ ቅሬታ መቀበልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መፍታት  ለባለስልጣኑ ከተሰጡ ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለፁት፣ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ዘመናዊ የመንገድ መብራት ተደራሽ በማድረግ፣ በምሽት ደህንነቱ የተጠበቀ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር በማስቻል፣ ውብ አካባቢን በመፍጠርና ከተማዋን በማዘመን ይዞት የመጣው እድል በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡  በዚህም ህብረተሰቡ ደስተኛ ነው፡፡ በተለያየ ጊዜያት የሚሰጠው ግብረ መልስ ለተቋሙ ብርታት እና ጥንካሬ ሆነውታል፡፡

የመንገድ መብራት ራሱን ችሎ ተቋም እንዲፈጠርለት የተደረገበት ዋና ዓላማ የከተማዋን የመልማት፣ የገፅታ ግንባታና የማህበረሰቡን የለውጥ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ነው፡፡  ሁሉም የከተማዋ ህብረተሰብ ደረጃቸውን የጠበቁ የመብራት አገልግሎቶች ማግኘት እንዲችል ጠንክረው እንደሚሰሩም ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ ሲመሰረት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ምን ይፈልጋል? ከተማዋንስ በምን መንገድ ነው ገፅታዋን ማስዋብ ያለብን ተብሎ ሲታሰብ፤ የመብራት አገልግሎት አንዱ እና ቀዳሚው መሆኑ ታምኖበት ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ሆኗል ሲሉም አክለዋል፡፡ 

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአንድ የፅህፈት ቤት ኃላፊና ሶስት ምክትል ኃላፊዎች የተዋቀረ ነው፡፡  ከዚህ ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ መብራት አገልግሎት ጥገናና ኦፕሬሽን ዘርፍ አንዱ እና የመጀመሪው ነው፡፡ ሁለተኛው በምክትል ዋና ዳይሬክተር ማዕረግ የግንባታና ኮንትራት አስተዳደር ዘርፍ፣ ሶስተኛው ደግሞ የደንበኛ አገልግሎት ዘርፍ ነው። አራተኛው የፅህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። የኃላፊዎች ሹመት ከተካሄደ በኋላ የሰራተኛ ቅጥር ተፈፅሟል፡፡ በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት 120 ሰራተኞች እንዳሉት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሰብስብ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ እየተዳደረ ያለው በፐብሊክ ሰርቪስ አዋጅ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት አዋጁን በመከለስ ከፐብሊክ ሰርቪስ ወጥቶ በቦርድ እንዲተዳደር በማድረግ ዘጠኝ የሚሆኑ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ለማፀደቅ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡

ተቋሙ ስራ ሲጀምር የራሱ የሆነ ህንፃ፣ የሰው ሃይል እንዲሁም የአሰራር መመሪያ አለመኖሩ ፈታኝ እንደነበር ያነሱት አቶ ሰብስብ፣ የደንበኛ አገልግሎት ዘርፍ፣ ጥገናና ኦፕሬሽን ዘርፍ፣ የጉዳት ካሳ እንዲሁም የተቋሙን የመተዳደሪያ ደንብና መመሪያዎችን በማዘጋጀትና በፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦ እንዲፀድቅ በማድረግ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡

ባለስልጣኑ የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በውጤታማነት ለመወጣት ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን፣ ከመብራት ሃይል አቅራቢ ተቋማት እንዲሁም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በቅንጅት ለመስራትም ስድስት የሚሆኑ ኮሚቴዎች ተቋቁሞ እየተሰራበት እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡ 

በኮሪደር ልማቱ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የመንገድ መብራቶች ከፍተኛ የማህበረሰብ ሀብት ፈሰስ የተደረገባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ መሰረተ ልማቶች ረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማህበረሰቡ በመጠበቅ እና በመንከባከብ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

በጥቅሉ በአዲስ አበባ ዘመናዊ የመንገድ መብራት አገልግሎት ለማዳረስ፣ ሲበላሹም በአፋጣኝ እንዲጠገኑ፣ እንዲጠበቁ በማድረግ፣ የከተማዋን ገፅታ ለመቀየር፣ በቀን ብቻ ሳይሆን በሌሊት ስራ የሚሰራባት እንድትሆን ስራውን በባለቤትነት የሚከታተል ራሱን የቻለ ተቋም መቋቋሙ ይበል የሚያሰኝ ነው። ተቋሙ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲችልም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል እንላለን፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review