AMN – የካቲት 11/2017 ዓ.ም
በ2017 በጀት ዓመት ያለፉት 6 ወራት ተደራሽ የተደረጉ የጤና አገልግሎቶች ውጤታማ እና ከእቅድ በላይ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው በበጀት ዓመቱ ያለፉ 6 ወራት በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ አበይት ክንውኖችን አስመልክቶ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ከ95 ሺህ በላይ እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል’ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ አገልግሎቶች ማግኘታቸውን ጠቁሟል፡፡
ቢሮው ከ5 ሺህ በላይ ሴት ወጣት ባለሙያዎችን በማሰልጠንና ወደ ስራ በማስገባት የቀዳማዊ ልጅነት የቤት ለቤት የወላጆች የምክር እና የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ማከናወኑን ገልጾ ከፅንስ እስከ 6 ዓመት የሆናቸው ህጻናት ጤናማ አካላዊ እና አዕምሯዊ እድገት እንዲኖራቸው፣ የስርዓተ ምግብ ልየታ፣ ክትባትና ሌሎች ክብካቤዎችን እንዲያገኙ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በዚህም 208 ሺህ 749 ህጻናት የእድገት ክትትል እንዲሰራላቸው መደረጉን ቢሮው አመልክቷል፡፡
ለ695 ሺህ 514 ህፃናት የፖሊዮ ክትባት ተደራሽ ማድረጉን ያመለከተው ቢሮው ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ደም ግፊት፡ ስኳር እና ተያያዥ በሽታዎችን አስመልክቶ 1 ሚሊየን 458 ሺህ 218 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የልየታ፡ የምርመራ እና የምክር አገልግሎቶችን ማግኘታቸውን ቢሮው አስታውቋል፡፡
በዚህም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እና የጤና ትምህርቶች ተደራሽ መደረጋቸውን ያወሳው ቢሮው በሁሉም የመንግስት ጤና ተቋማት ነጻ የምርመራ ኮርነር በማዘጋጀት አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ 6 ወራት ተመላላሽ ህክምናን አስመልክቶ 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ለሚሆን ጊዜ አገልግሎት መስጠጥ መቻሉን ቢሮው አስታውቋል፡፡
የአስተኝቶ ህክምናን በተመለከተ ለ121 ሺህ 165 ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት መሰጠቱን ያመለከተው ቢሮው የአስተኝቶ ህክምና ታካሚዎች ሞት ምጣኔ ከ1 ነጠብ 2 ከመቶ በታች ማድረስ መቻሉን አመልክቷል፡፡
የፅኑ ህሙማን የሞት ምጣኔን ከ23 በመቶ በታች ማድረስ መቻሉን ያመለከተው ቢሮው የህክምና አገልግሎቶች ጥራት አስመልክቶ የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን መስፈርት እና ሀገራዊ ዓላማን ማሳካት መቻሉን ጠቁሟል፡፡
በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራም የታቀፉ አባላት ቁጥርም 2.5 ሚሊየን ማድረስ መቻሉን አውስቷል፡፡
1 ሚሊየን 330 ሺህ 562 የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ አባላት እና ቤተሰቦቻቸው በጤና ጣቢያዎች፣ በሪፈራል እና ስፔሻላዝድ ሆስፒታሎች አገልግሎት ማግኘታቸውንም ቢሮው አመልክቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ 51 ጤና ተቋማት የጤና መረጃ ስርዓታቸውን በሙሉ ወረቀት አልባ ማድረጋቸውንም አስታውቋል፡፡
በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ባለቤትነት ለማረጋገጥና ተገልጋይ ተኮር ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር የህብረተሰብ ምዘና ስርአት በሁሉም ጤና ጣቢያዎች መተግበሩን አመልክቷል፡፡
በዚህም ከተገልጋዩ ጋር ቋሚ የግንኙነት መድረክ በመፍጠር፣ ህብረተሰቡ በራሱ ተቋሙን የሚመዝንበት እና ሃሳቦችን የሚያቀርብበት አሰራር በመዘርጋት በየጤና ተቋማቱ ተጨባጭ ለውጦችን እያስገኘ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል።
በሰለሞን በቀለ