ባለፉት 6 ወራት ከ 8 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ወደ ቫት ስርዓት እንዲገቡ ተደርጓል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ባለፉት 6 ወራት ከ 8 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ወደ ቫት ስርዓት እንዲገቡ ተደርጓል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN-የካቲት 12/2017 ዓ.ም

ባለፉት 6 ወራት ከገቢ ስራ አንፃር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ስርዓት ውስጥ መግባት እየተገባቸው ያልገቡ 8 ሺህ 450 የንግድ ተቋማት ወደ ቫት ስርዓት እንዲገቡ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በዚህም የታክስ ኦዲት ሽፋን እና ውጤታማነት ለማሻሻል እንዲሁም ለማስፋት በተሰራው ስራ በመርካቶ እና በከተማዋ በሚገኙ ትልልቅ የንግድ ቦታዎች የተሰራው የቁጥጥር እና ህግ የማስከበር ስራ ገቢ ከማሳደግ ባሻገር ፍትሃዊነት እንዲሰፍን አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም 4ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በጉባኤው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገቢን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ባለፉት 6 ወራት 125.5 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 111.5 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል ብለዋል።

የገቢ አሰባሰቡ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው 74.3 ቢሊየን ብር ጋር ሲነፃፀር በ37.2 ቢሊየን ብር ወይም በ50 በመቶ ምርታዊ እድገት ማሳየቱንም ጠቁመዋል።

ባለፉት 6 ወራት የከተማ አስተዳደሩን ሀብት አመዳደብ እና አጠቃቀም ውጤታማነትን ለማሳደግ በተደረገው የበጀት ድልድል፣ የከተማ አስተዳዳሩን የትኩረት አቅጣጫዎች በመለየት ለዘላቂ ልማት ዘርፎች እና የህዝቡን የኑሮ ጫና ለሚቀንሱ የልማት ስራዎች እንዲደለደል መደረጉንም አንስተዋል።

በዚሁ መሰረት ለዘላቂ ልማት የሚመደበውን የመንግስት በጀት በ2016 ዓ.ም ከነበረበት 60 በመቶ ወደ 63 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ አፈፃፀሙ 71 በመቶ መድረስ ችሏል ብለዋል።

ይህም ለመደበኛ ብር ከ29 ቢሊየን 049 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም ለካፒታል ከ 64 ቢሊየን 188 ሚሊየን ብር በላይ በድምሩ ከ93 ቢሊየን 237 ሚሊየን ብር በላይ ይህም 98.39 በመቶ ክፍያ መፈፀም የተቻለ ሲሆን አፈፃፀሙም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 41.1 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል።

የገቢና ወጪ መጣጣም እና እድገቱ፣ ከተማዋ ምን ያህል በፈጣን ለውጥ ውስጥ እንደሆነች አንዱ ተጨባጭ ማሳያ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር የበጀቱ 71 እጁ ለዘላቂ ልማት፣ ድህነት ለመቅረፍ እና የህዝቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል መዋሉ ምን ያክል ለከተማዋ ነዋሪዎች ትኩረት እንደተሰጠን እና በታማኝነት እያገለገልን እንደሆነ የሚያሳይ ሌላው ተጨባጭ ማስረጃ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review