AMN-ጥር 7/2017 ዓ.ም
ባለፉት ስድስት ወራት ከ721 ሺህ በላይ የተለያዩ ፓስፖርት ተዘጋጅቶ ለዜጎች መሰራጨቱን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ይህ ከአምናው ተመሳሳይ የበጀት ዘመን ጋር ሲነፃፀር የ31 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ገልጸዋል፡፡
ከተሰራጩ ፓስፖርቶች በተጨማሪ ተቋሙ በግማሽ ዓመቱ የአስቸኳይ ፓስፖርት አገልግሎትን ከዋና መስሪያ ቤት በተጨማሪ በክልል በሚገኙ 7 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ማለትም በደሴ፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ ባህርዳር፣ ድሬደዋ፣ አዳማ እና ሆሳዕና ቅርንጫፍ ላይ መስጠት መቻሉን ዋና ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።
በዋና መስሪያ ቤትና በቅርንጫፎች በሳምንት ከ3 ሺ 400 በላይ አስቸኳይ ፓስፖርት አመልካቾችን ማስተናገድ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል አገሪቱን የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ማዕከልነት ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከፍ ለማድረግ 188 ሀገራት የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት የማስተናገድ አቅማቸው እየተሻሻለ መምጣቱን በዚህም በአየርና በየብስ ከ3.3 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ መንገደኞች አገልግሎት መሰጠት መቻሉን መግለጻቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያሳያል።