ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ የነበሩ ከ92 ሺ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ
AMN – ሚያዝያ 09/2017
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ የነበሩ ከ92 ሺ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በዘንድሮው ዓመት የእስካሁን ዘጠኝ ወራት በውጭ ግንኙነት ዘርፍ ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ያስቻሉ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን አንስተዋል።
በዚህ ረገድ በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በተከናወኑ ጥረቶች በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ይገኙ የነበሩ 92 ሺህ 43 ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስታውቀዋል።
የዜጎችን ደህንነትና ክብር የማስጠበቅ ስራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀዳሚ ኃላፊነት ነው ያሉት ቃል አቀባዩ አምባሳደር ነብያት፣ አሁንም በማይናማር እንዲሁም በሌሎች ሀገራት ውስጥ ሆነው አስከፊ ህይወት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የመታደግና ወደ ሀገራቸው የመመለስ ጥረት ተጠናክሮ ስለመቀጠሉም አስታውቀዋል።
ጎረቤት ሀገራትን ባስቀደመ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና መርህ ጥላ ስር የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብሮችን ለማጠናከር በትኩረት መሰራቱንም አምባሳደር ነብያት ጠቅሰዋል።
በዚህም በዘጠኝ ወራት ውስጥ 11 ስምምነቶች ከተለያዩ ሀገራት ጋር ተፈርመው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቀዋልም ብለዋል።
533 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና አልሚዎች ወደ ሀገር ውስጥ መጥተው የኢንቨስትመንት አዋጪነት ጉብኝት ስለማድረጋቸው አምባሳደር ነብያት በመግለጫቸው አንስተዋል።
በአቡ ቻሌ