ባለፉት የለውጥ አመታት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሰዎችን ቁጥር 74 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል – ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)

You are currently viewing ባለፉት የለውጥ አመታት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሰዎችን ቁጥር 74 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል – ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)

AMN – ታኀሣሥ 21/2017 ዓ.ም

ባለፉት የለውጥ አመታት በተሰራው ስራ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሰዎችን ቁጥር ወደ 74 ሚሊዮን ማሳደግ መቻሉን የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ እንደገለጹት ባለፉት የለውጥ አመታት ህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በለውጥ አመታቱ 25 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፤ በዚህም የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ወደ 74 ሚሊዮን ማሳደግ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

መንግስት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚውን ህብረተሰብ በከተማም ሆነ በገጠር አካባቢዎች ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማና ትልቅ ስኬት የተገኘባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በኢነርጂ ዘርፉም ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የተከናወነውን ስራ እና የተገኘውን ትልቅ ስኬት አንስተዋል።

የህዳሴ ግድብ በትልቅ ቁጭት የተጀመረ ቢሆንም ከለውጡ በፊት በገጠመው መሰናክል ስራው ወደማይሰራበት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር አንስተው በለውጡ አመታት በተወሰደው ትልቅ እርምጃ ፕሮጀክቱ ወደማጠናቀቂያ ምዕራፍ በመድረሱ ትልቅ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።

በአማራጭ የሃይል አቅርቦት በኩልም እንዲሁ ሀይል በማይደርስባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በድርቅ እና በጎርፍ ይከሰት የነበረውን የአደጋ የተጋላጭነት ለመቀነስ መንግስት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ በትኩረት መስራቱንም ሚኒስትሩ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም ድርቅ እና የጎርፍ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉትን ከፍተኛ ጉዳት ማስቀረት መቻሉን ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ ቀጣናውን በሀይል ለማስተሳሰር ከፍተኛ ስራ እየሰራች መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ይህም ከራስ አልፎ ጎረቤት ሀገራትን ጭምር ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰራው ስራ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።

May be an image of 1 person

All reactions:

2121

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review