AMN – ጥር 13/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ባለፋት 6 ወራት በተከናወኑ እቅዶች ዙሪያ ከሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር እየገመገመ ይገኛል፡፡
አዲስ አበባ ከተማን ከደንብ ጥሰት የጸዳች ለማድረግ በተሰራዉ ዉጤት ተመዝግቧል ሲሉ በመድረኩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ተናግረዋል፡፡
ከተማዋ የጀመረችዉ የኮሪደር እና ሌሎች የልማት ስራዎች ሴኬታማ ለማድረግ 27 ተቋማትን በማቀናጀት ሰፊ ስራዎች መከናወናቸዉን አንስተዋል።
ህገወጥ የመሬት ወረራ፣ ህገወጥ ግንባታ፣በትምህርት ቤቶች አከባቢ አዋኪ ድርጊቶችን በመቆጣጠረና ህግና ስርአት በከተማዋ እንዲነግስ ለማስቻል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዉጤታማ ስራ ማከናወን መቻሉንም ገልጸዋል።
ይህንን ለማስቀጠልም ከተቋማት ጋር የጀመረዉ ቅንጅታዊ ስራን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ባለፉት ወራት በረካታ የሪፎረም ስራዎችን ተቋሙ ማከናወኑን ተናግረዋል ።
በዚህም በከተማዋ የነበረውን የደንብ ጥሰት ባለፋት 6 ወራት ከ 56 በመቶ በላይ እንዲቀንስ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ህገወጥ ተግባራትን በመከላከል ረገድም እስከ ታህሳስ ወር ከ135 ሚሊየን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ መደረጉንም አንስተዋል።
በሩዝሊን መሀመድ