AMN – ኅዳር 10/2017 ዓ.ም
ባሳለፍነው ሩብ ዓማት የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ለማቃለል ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ከንቲባዋ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከንቲባዋ በሰጡት ማብራሪያም ባሳለፍነው ሩብ ዓማት ከሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ከ2 ሺህ 780 በላይ የደሀ ቤቶች ተገንብተው አረጋውያን ሴቶች እና አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ባለሀብቶችን በማሳተፍ ማዕድ ማጋራት መቻሉን ከንቲባዋ ጠቁመዋል።
ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በቀን 1 ሺህ የሚሆኑ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች የሚመገቡበት የምገባ ማዕከል መገንባት መቻሉን እና ለ4 ሺህ ዜጎችም ምቹ መኖሪያ አካባቢ እንዲያገኙ መደረጉን አብራርተዋል።
በነገዋ የልህቀትና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ለመጀመሪያ ጊዜ 320 ተጋላጭ የነበሩ ዜጎችን በማሠልጠን በማብቃት እና መቋቋሚያ በመስጠት ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህም ማዕከሉ ከከተማዋ ባለፈ ለሌሎች ከተሞችም ተደራሽ የመሆን አቅም እንዳለው ማየት ተችሏል ብለዋል።
የሴቶችን ተጋላጭነት እና የእናቶችን ጫና ለመቀነስ በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም 360 ሺህ ሕፃናትን በማቀፍ ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ መሠራቱን እና ገቢ እያላቸው የግንዛቤ ችግር ላለባቸውም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከ5 ሺህ 200 ወጣቶችን በማሠልጠን እና በማብቃት በየመኖሪያ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው እንደ ጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
አንድ ሺህ የሕፃናት ማቆያዎችን ማዘጋጀት መቻሉን እና እሑድ እሑድ አየተዘጉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው መንገዶችን ጨምሮ ወደ 900 የሚጠጉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲኖሩ ማድረግ መቻሉንም ከንቲባዋ አብራርተዋል።
ከኮሪደር ልማት ተነሺዎች ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት ችግር እንዳያጋጥም አማራጭ ትራንስፖርቶችን ማቅረብ መቻሉን እና ከመንገድ ግንባታ አንፃርም አጋጥሞ የነበረውን የግንባታ መጓተት በመፍታት በሌሎች ኮንትራክተሮች መንገዶቹ በፍጥነት እንዲገነቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በከተማ አንዳንድ አካባቢዎች አሉ ከተባለው የፈረቃ ትምህርት አንፃር ከምክር ቤት አባላት ለተነሡ ጥያቄዎች በከተማ ደረጃ 12 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን እና 43 ትምህርት ቤቶችን የማደስ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከምገባ ከትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት እና እየታዩ ካሉ መሻሻሎች አንፃር የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የስበት ማዕከል እየሆኑ መጥተዋል።
ይህንንም ተከትሎ መካከለኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ከግል ትምህርት ቤቶችም ጭምር በማውጣት በማስመዝገባቸው እንዲሆም በኮሪደር ልማቱ ምክንያት የመኖሪያ አካባቢ የቀየሩ ተማሪዎች ከመኖራቸው አንፃር ችግሩ መፈጠሩን እና ችግሩን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።
በሽመልስ ታደሰ