ብልጽግና ፓርቲ በአጭር ጊዜያት ወስጥ ኢትዮጵያን ከተረጅነት በማላቀቅ ወደ ተሟላ ሉዓላዊነት ለማሸጋገር የሚያስችሉ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ።
ፓርቲው ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
አቶ አደም ፋራህ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተገኙ ስኬቶች እና የወደፊት ትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል፡፡
በዚህም ህዝብ ሲያነሳቸው የነበሩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች ለውጡ እንዲመጣ ያደረጉ ገፊ ምክንያቶች ስለመሆናቸው አብራርተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ መሪነት የለውጡ መንግስት የኢትዮጵያን ታሪካዊና አሁናዊ ችግሮች በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በቂ ትንተና አድርጎ ወደ ስራ ስለመግባቱም አስረድተዋል፡፡
በተለይ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር ፓርቲው በግንባር አርአያ በመሆን ጭምር በርካታ ስራዎችን ማከናወኑንም አንስተዋል።
ለአብነትም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በአብላጫ ድምጽ አሸንፎ መንግስት የመመስረት ህገ-መንግስታዊ መብት ቢያገኝም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተለያዩ የአመራር ደረጃዎች ላይ ማሳተፉን አስታውሰዋል።
ይህም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ አዲስ ምእራፍ የከፈተ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር፣ ማህበራዊ ልማትን በማጎልበት፣ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሰጠና ትብብር ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲን ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሏንም ተናግረዋል።
ከልመናና ተረጅነት በመላቀቅ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይገባል በሚል መርህም ተስፋ ሰጪ የኢኮኖሚ ልማት ስራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ብልጽግና ፓርቲ ለማህበራዊ ልዕልና፣ ለተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት እንዲሁም ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራቱን ተናግረዋል።
በዚህም ፓርቲው ለሰላማዊ መፍትሄ ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ በተግባር ማረጋገጡን ጠቅሰው፤ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በማሳያነት አንስተዋል፡፡
በአፍሪካ ግዙፍ ፓርቲ የሆነው የብልጽግና ፓርቲ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካዊ እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር ለፍትሃዊ እና የጋራ ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘገቧል።
በቀጣይም ፓርቲው መሰል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ አደም ፋራህ አመላክተዋል፡፡