ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያውያንን በሰፈር ሳይከፋፍል አቅፎ የያዘ ፓርቲ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ብልጽግና ፓርቲ በብዙ መንገድ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ፓርቲዎች ይለያል ሲሉ ገልጸዋል።
በአደረጃጀጀቱ፣ በእሳቤው እና በሚያስገኛቸው ለውጦች ከሌሎቹ የሚለይባቸው መገለጫዎች እንደሆኑ አመልክተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በሰፈር ሳይከፋፍል ኢትዮጵያውያንን አቅፎ የያዘ ብቸኛ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ከፓርቲው ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ የነበረውን እድገት ጨምሮ አሁን ላይ 16 ነጥብ 3 ሚሊዮን አባል ያለው ፓርቲ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በአፍሪካ ትልቁ ፓርቲ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለን ያቀፈ መሆኑ፣ ካለው ስፋትም ባሻገር ትልቅ ራዕይ እና ግልጽ የሆነ አሰራርና ስርዓት ያለው መሆኑን ነው የገለጹት።
የፓርቲው ስያሜም ኢትዮጵያን የብልጽግና ማማ ላይ ለማድረስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ከተያዘው ራዕይ ጋር የተጋመደ መሆኑን ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለሁሉም ክፍት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመንግስት ስልጣን ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረጉ የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።
ወጣቶች እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች አቅፎ የያዘ መሆኑን ጠቅሰው ፓርቲው አዲስ እሳቤ እና አመለካከት የመቀበል ችግር እንደሌለበት አመልክተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በብዙ መንገድ ተስፋ የሚጣልበት በአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን በአደረጃጀቱ፣ ባለው ስፋት፣ ራዕይ፣ ስያሜ እና ግብ ከሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።