ብልጽግና ፓርቲ እና የተርኪዬ ጀስቲስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት (ኤኬ ) ፓርቲ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

You are currently viewing ብልጽግና ፓርቲ እና የተርኪዬ ጀስቲስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት (ኤኬ ) ፓርቲ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

AMN-ጥር 22/2017 ዓ.ም

ብልጽግና ፓርቲ እና የተርኪዬ ጀስቲስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት (ኤኬ) ፓርቲ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ዛፈር ሲራካያን በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመታደም አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ፥ የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ዛፈር ሲራካያን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ከውይይቱ ባለፈ በኢትዮጵያና ተርኪዬ መካከል በተለያዩ መስኮች ያለውን ትብብር ለማጠናከር በመርሆች ላይ የተመሰረተ የጋራ መድረክ ለመፍጠር በብልጽግና እና ኤኬ ፓርቲዎች መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ እና የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ዛፈር ሲራካያን የመግባቢያ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ የጋራ ፖለቲካዊ ትብብር ለመፍጠር በመሪዎች ደረጃ ግንኙነት መመስረትና ሀሳብ ለመለዋወጥ፣ የትምህርትና አቅም ግንባታ፣ የሴቶችና ወጣቶችን የጋራ የሁለትዮሽ መድረክ ማዘጋጀትን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ያማከለ በጤና፣ በግብርናና ባህልና ቱሪዝም ዘርፎች እንዲሁም የንግድና ምጣኔ ሀብት ትስስር መፍጠር እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም የተዛቡ መረጃዎችን በመመከት የጋራ መግባባት እና የመረጃ ልውውጥን ለማቀላጠፍ የሁለትዮሽ ትብብር መመስረት ያስችላልም ተብሏል።

በጋራ ጉዳዮች ላይ መድረኮችን በማዘጋጀት በአለም አቀፍ መድረኮች ምክክርና ትብብርን ማዳበር፣ ወቅታዊ መረጃ መለዋወጥ፤ በጋራ እና በባለብዙ ወገን አጀንዳዎችና ተግዳሮቶች መተባበርና መደጋገፍን ያለመ እንደሆነም ኢዜአ ዘግቧል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ እና ለመቋቋም የታዳሽ ኃይልና አረንጓዴ ቴክኖሎጂ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብትና ብዝሃ ህይወትን በጋራ መጠበቅን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review