AMN – ታኀሣሥ 21/2017 ዓ.ም
ብሔራዊ ቤተ መንግስት ውብ ኪነ ህንጻ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የታሪክ መረጃ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ተናገሩ፡፡
እድሳቱ የተጠናቀቀው ብሔራዊ ቤተ መንግስት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፣ ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና እንግዶች በተገኙበት ተመርቆ ለህዝብ ክፍት ሆኗል፡፡
ብሔራዊ ቤት መንግስት ውብ ኪነ ህንጻ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የታሪክ መረጃ መሆኑን ነው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተናገሩት፡፡
ንጉሰ ነገስቱ ቤተ መንግሰቱን ሲገነቡ መነሻ የሆናቸው ዘመናዊነትን መገንባት፣ ወደ ጥንካሬ መመለስን ማሳየት እና አዲስ አበባ ከተማን የነጻነት ተምሳሌት እና አለም አቀፍ መዲና ለማድረግ በመሻት ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ቤተ መንግስቱ የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት መስተጋብር ጎልቶ የሚታይበት መሆኑንም ነው ፕሬዝዳንት ታየ የገለጹት፡፡
በተለያዩ የመንግስት ስርዓቶች ለውጥ ውስጥ ቤተ መንግስቱ የያዛቸውን ሀብቶች ይዞ እንዲቆይ በታማኝነት ለጠበቁ አካላት ምስጋና ያቀረቡት ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ቤተ መንግስቱ በሚገባው ልክ ለህዝብ እይታ እንዲበቃ መደረጉም ያለውን ታሪካዊ ፋይዳ በመረዳት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እድሳቱ የተጠናቀቀው ብሔራዊ ቤተ መንግስት እና በውስጡ የያዛቸው የቅርሶች ስብስብ ሙዚየም ለህዝብ እይታ ክፍት ሆኗል፡፡
በሰብስቤ ባዩ