- ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 አባላት ያሉት ብሪክስ ፕላስ በፈረንጆቹ 2025 በሚያካሄደው ጉባኤ 9 ጨማሪ ሀገራትን አባል ያደርጋል ተብሏ
“ድህነት በአፍሪካ ምድር ላይ የተቆፈረ ጥልቅ ጉድጓድ ነው፤ ልክ እንደ ቤርሙዳ ትሪአንግል ብዙዎችን ውጦ ያስቀረ” ይላል ቦትስዋናዊው ገጣሚ ኬኔት ማስዋቢ። “አፍሪካ ለምን ድሃ ሆነች የሚለውን እንደ ታዋቂዋ ኢኮኖሚስት ዳምቢሳ ሞዮ ውስጠ ምስጢሩን የገለጠው የለም” እያሉ ብዙዎች ይመሰክሩላታል። ዳምቢሳ ሞዮ “እኛ አፍሪካውያን ያልተረዳነው ዋናው ነገር አፍሪካ ወደ ከፍታ የምትሻገረው በእርዳታና በሌሎች ችሮታ ሳይሆን በጠንካራ የሥራ ባህል፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና በካፒታል ነው” ስትል ‘ዴድ ኤይድ’ በተሰኘው መፅሐፏ ትሞግታለች፡፡
‘ሞዮ’ የሚለው ቃል የስዋሂሊ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ‘ልብ’ ማለት ነው። በርግጥም ዳምቢሳ ሞዮ አፍሪካ ስለድህነቷ ምንጭ እና መፍትሄ ብዙ ልብ ማለት ያለባትን ጉዳዮች በበቂ ማስረጃዎች በመፅሐፏ አስቀምጣዋለች። አፍሪካን ለድህነት ከዳረጓት ምክንያቶች መካከል ሁሉንም በእኩልነት የማያየው የአለም የአስተዳደር ሚዛን እና ይህንን ለማስጠበቅ በቆሙ ተቋማት ተፅዕኖ እንደሆነም ጠቅሳለች። ብሪክስ ደግሞ የአለምን የተዛነፈ ሚዛን ለማስተካከል የመጣ ድንቅ አማራጭ መሆኑን በርካታ ጥናቶች እያመላከቱ ሲሆን በዚህ ትንታኔ ብሪክስ ለአፍሪካ ምን ይጠቅማል? የሚለውን እንፈትሻለን፡፡
የብሪክስ አባል ሀገራት 42 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ እና ከሩብ በላይ የምድሪቱን አጠቃላይ ምርት ይሸፍናሉ፡፡ የብሪክስ መስራች ሀገራት ደግሞ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ የሚጫወቱት ሚና በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ መረጃ ከሆነ የብሪክስ መስራች ሀገራት (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድ) የአፍሪካ ዋና ኢኮኖሚ በተለይም የንግድ አጋር ናቸው፡፡

በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የቻይና[1]አፍሪካ የምርምር ተቋም (ሲ.ኤ.አር. አይ)፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የቻይና ልማት ባንክ በቅርቡ ያወጡት መረጃ እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ በ2023 ቻይና በአፍሪካ ልማት ውስጥ በትልቅ ልማቶች ላይ ተሳትፎዋን አጠናክራ ቀጥላለች። ይህንንም ተከትሎ የቻይና ኢንቨስትመንቶች በቅርብ ዓመታት በአፍሪካ ከ20 እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ በዓመት ከፍ ብሏል፡፡
በ2013 የተጀመረው የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የቻይና ኢንቨስትመንቶችን በአፍሪካ ለማሳደግ እንደ ማዕከላዊ ሀይል ሆኗል፡፡ ቻይና በአፍሪካ ውስጥ መሠረተ ልማት መንገዶች፣ ባቡር፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና ወደቦች ግንባታ ላይ በስፋት እየተሳተፈች ነው። በኢነርጂ ዘርፍም እያደረገች ያለችው ልማት በጉልህ የሚጠቀስ ነው፡፡ ለአብነትም ዘይት፣ ጋዝ እና የታዳሽ የኃይል ፕሮጀክቶች (ለምሳሌ የውሃ፣ የፀሐይ እና የንፋስ ሃይልን በሚያመንጭ ኢንቨስትመንቶች ላይ ይበልጥ አተኩራለች፡፡
ቻይና በአፍሪካ ከተሳተፈችባቸው ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች አንዱ ማዕድን ማውጣት ነው። በዚህም የቻይና ኩባንያዎች እንደ መዳብ፣ ኮባልት፣ ወርቅ እና መሰል የማዕድን ሃብቶች ላይ በስፋት ተሰማርተዋል። ማኑፋክቸሪንግ እና ኢንዱስትሪ ላይም በቀላል ማምረቻ፣ ጨርቃ ጨርቅ እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች የአፍሪካን የምርት አቅም እያሳደጉ ስለመሆኑም በመረጃዎቹ ተመላክቷል፡፡
የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም እ.ኤ.አ ሰኔ 20 ቀን 2024 “ኋይ ስትሮንግ ሪጅናል ቫሉይ ቼይንስ ዊል ቢ ቫይታል ቱ ዘ ኔክስት ቻፕተር ኦፍ ቻይና ኤንድ አፍሪካስ ኢኮኖሚክ ሪሌሽንሺፕ” በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ባለፉት 20 ዓመታት ቻይና ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ወሳኝት የሁለትዮሽ የንግድ አጋር ሆናለች። ከአካባቢው የወጪ ንግድ 20 በመቶው ወደ ቻይና የሚሄድ ሲሆን፣ 16 በመቶው የአፍሪካ ምርቶች ከቻይና እንደሚመጡም የአለም የገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ)ን ዋቢ አድርጎ ገልጿል።
ይህም በ2023 በጠቅላላ የንግድ ልውውጥ 282 ቢሊዮን ዶላር ሪከርድ ነበረው የሚለው መረጃው፣ ዋና ምርቶቹም ብረታ ብረት፣ የማዕድን ውጤቶች እና ነዳጅ ናቸው፡፡ አፍሪካ ወደ ቻይና ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ ሶስት አምስተኛውን የሚወክሉ አፍሪካም የቻይና ማምረቻ ዕቃዎች፣ ኤሌክትሮኒክስ እና ማሽነሪዎችን ታስገባለች። እንደ መረጃው ከሆነ አፍሪካ በ2063 የያዘቻቸውን የልማት አጀንዳዎች ለማሳካት ቻይናን የመሳሰሉ ሀገራት ወሳኝ የልማት አጋር ሆነው ቀጥለዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ስታንዳርድ ባንክ በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው በአፍሪካ ውስጥ የብራዚል ኢንቨስትመንት መጠን 10 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ የብራዚል ዋና መዋዕለ ንዋይ ግብርና፣ ዘይት፣ ማዕድን፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች እንዲሁም የባዮ ኢነርጂ ምርት እና በሌሎቹም ዘርፎች ላይ እየዋለ ነው።
የአፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም፣ ብሪክስ ለአፍሪካ ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ እ.ኤ.አ ጥቅምት 28 ቀን 2024 ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመላክተው ብሪክስ ለአፍሪካ ሀገራት እንደ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ዘላቂ ልማት ባሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ትብብር ለማድረግ ጠቃሚ መድረክ ነው፡፡ ሁሉን አካታች እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተው የብሪክስ ጥምረት ለአፍሪካ ሀገራት በአለም አቀፍ የኢኮኖሚ አስተዳደር ውስጥ ያላቸውን ሚና ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ወሳኝ አጋጣሚ ነው ይላል መረጃው፡፡
ብሪክስ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን አፍሪካም ለብሪክስ መስራች ሀገራት ጉልህ የሆነ ጠቀሜታ እንዳላት በመረጃው የተካተተ ሲሆን፣ ለአብነትም የብሪክስ ዋና መስራች ሀገራት በአፍሪካ ውስጥ እንዲሳተፉ ካደረጋቸው ምክንያቶች መካከል በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ኢኮኖሚን ለመመስረት ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት፣ አፍሪካ ሰፊና ያልተጠቀመችበትን የግብርና ዘርፍ ወደ ልማት በመቀየር የበለጠ የሚጠቀሙበት ዕድል ስላለ እንዲሁም ኢንቨስት ለማድረግ፣ የቴክኖሎጂ የእውቀት ሽግግር በተሳካ መልኩ ለማከናወን አፍሪካ ምቹ በመሆኗ ተመራጭ መዳረሻቸው እንዳደረጓት በመረጃው ተመላክቷል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ የብሪክስ ሀገራት ከአምስት አባላቶቻቸው በላይ ትብብራቸውን ለማስፋት ያላቸውን ፍላጎት በማሳየት ረገድ ተሳክቶላቸዋል የሚለው መረጃው ለአብነትም ከ2023 ጀምሮ ኢትዮጵያ፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ግብፅ የብሪክስ ህብረት አባል እንደሆኑ ጠቅሷል፡፡
በብሪክስ ሀገራት መካከል የተወጠነው “አንድ ወጥ ገንዘብ ማቋቋም” የሚለው ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ ብቻ አይደለም የሚለው ጥናቱ ጉልህ ጂኦፖለቲካዊ እንድምታዎች እንዳሉትም ጠቆም አድርጎ አልፎታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ምንዛሪ መተግበር የዓለምን የፋይናንስ ኃይል ድልድል ሊለውጥ ይችላል የሚለው መረጃው በዩ.ኤስ.ኤ እና በአውሮፓ ኅብረት የበላይነት የሚዘወሩ የኢኮኖሚ ማዕከላት ወደ ትክክለኛ፣ ሚዛናዊ፣ አካታችና ፍትሃዊ መስመር እንዲገቡ አስገዳጅ ሁኔታን የሚፈጥር አሊያም ሁሉን ያካተተ እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አዲስ መስመር እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው፡፡
በመሆኑም በብሪክስ ምንዛሪ ሊመጣ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ጂኦፖለቲካዊ አንድምታ በመመርመር፣ ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴን፣ የፋይናንሺያል መረጋጋትን እና በአለም አቀፍ የገንዘብ ስርዓቶች ውስጥ ያለውን የሃይል ሚዛን በእጅጉ የሚቀይር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በማመላከት ይህም ለአፍሪካ አዲስ አማራጭ እንደሚሆን አለም አቀፍ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምሁራን እየገለፁ ነው፡፡ እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ መረጃ ከሆነ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብሪክስ ዋና መስራች ሀገራት በአፍሪካ ያላቸውን ተሳትፎ አስፋፍተዋል። የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና የንግድ መጠን ላይ ያላቸው ድርሻ በፍጥነት ከፍ ብሏል።
ለአብነትም በህንድ እና በአፍሪካ መካከል ያለው አጋርነት በአህጉሪቱ ውስጥ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን እድገት እንዲያስመዘግቡ አድርጓል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ብራዚል እና ሩሲያ በአፍሪካ በማዕድን እና በኢነርጂ ኢንዱስትሪ በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ በውጤት ምዕራፍ ላይ ናቸው፡፡ የብሪክስ አባል ሀገራት መንግስታት እና ባለሀብቶቻቸው በአፍሪካ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ እና በአገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡
የብሪክስ ሀገራት ያላቸውን ልምድ እና ሁለንተናዊ አቅም በማሰባሰብ በአፍሪካ የግብርና ዘርፍ ላይ በስፋት በመሰማራት እና ልምዳቸውንም በማካፈል ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉበት ዕድል አለ የሚለው መረጃው፣ ለአብነትም ብራዚል የግብርና ልማትን በተመለከተ ለአፍሪካ ሀገራት አርአያ መሆን ትችላለች። የአፍሪካን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ እና የምግብ ዋስትና እጦት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ሰፊ ድጋፍ ታደርጋለች፡፡
ስለሆነም ብሪክስ ከተነሳበት፣ በፍትሃዊነት አብሮ የማደግ አላማ አንፃር በአፍሪካ ግብርናን በማሳደግ ድህነትን እና ረሃብን በዘላቂነት ለማጥፋት ዋነኛ የልማት መሳሪያ ይሆናል የሚለው መረጃው፣ ለዚህ ስኬት ደግሞ የብሪክስ አባል ሀገራት አቅም፣ ልምድና ተሳትፎ ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸውም ተመላክቷል፡፡
የብሪክስ መስራች ሀገራት በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ በስፋት መሳተፋቸው ብዙ ጥቅሞችን ያስገኝላቸዋል የሚለው መረጃው ለአብነትም ከአንድ ቢሊዮን በላይ አፍሪካዊ ሸማቾችን የማግኘት ዕድል አላቸው፡፡ በሌላ በኩልም አፍሪካ በተመጣጣኝ ዋጋ በቂ ምርት ከውጭም ከውስጥም እንድታገኝ ያስችላታል፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች እና ንግድን በመሳሰሉ ዘርፎች በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ዕድገት እየተመዘገበ ነው፡፡
ብሪክስ ለአፍሪካ እንደ ማዕድን፣ ትራንስፖርት፣ ንፁህ ኢነርጂ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች እና ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂን በመሳሰሉ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ጠቃሚ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምንጭ ሆኗል፡፡ በመሆኑም የብሪክስ ጥምረት ለአህጉሪቱ አዳዲስ የዕድገት በርን እየከፈተ ስለመሆኑም ተብራርቷል፡፡
በመለሰ ተሰጋ