AMN-ጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም
በመጀመሪያ እና ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች ተማሪዎች ስልክ እንዳይጠቀሙ በሚገድበው ሕግ ላይ የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ፊርማቸውን በረቂቅ ህጉ ላይ አኑረዋል፡፡
የብራዚል ትምህርት ሚኒስትር ካሚሎ ሳንታና ልጆች በሕጻንነታቸው ስልክ በመያዝ ከዕድሜያቸው ጋር ላልተጣጣመ መረጃ ይዳረጋሉ ብለዋል፡፡
ማህበራዊ ሚዲያው ከሚያሳድርባቸው ጫና አንጻር አስተዳደጋቸውን ለመከታተል ለወላጆች አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረው አዲሱ ህግ ይህን እንደሚቀርፍ አስታውቀዋል፡፡
በመጀመሪያ እና በከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች ተማሪዎች ስልክ እንዳይጠቀሙ ገደብ የሚጥለው አዲሱ ረቂቅ ህገ ለአስገዳጅ ሁኔታዎች ብቻ ስልክ መጠቀምን የሚፈቅድ ነው ተብሏል፡፡
ለድንገተኛ አደጋዎች፣ በመምህራን መሪነት ለትምህርት ጉዳዮች እና ስልክ መያዝ አስገዳጅ ለሚሆናቸው አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ህጉ ይፈቅዳል፡፡
ህጉ ከፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ግራ ክንፍ ፓርቲ ፖለቲከኞችም ሆነ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጄር ቦልሶናሮ ቀኝ ዘመሙ ፓርቲ እምብዛም ድጋፍ አለማግኘቱ ተገልጿል፡፡
በአንጻሩ በበርካታ ወላጆችና ተማሪዎች በኩል በጎ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
በረቂቁ ላይ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ላይ የተሳተፉ ከ66 በመቶ በላይ የሚሆኑት ስልክ ከተማሪዎችና ከታዳጊዎች ለማራቅ በመንግስት በኩል የተደረሰው ውሳኔ ተገቢ ነው ማለታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡