AMN – የካቲት 8/2017 ዓ.ም
ተለዋዋጭ ከሆነው የዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጋር በፍጥነት ለመራመድ አፍሪካዊያን በጋራ መቆም እንደሚገባቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ገለጹ፡፡
ሊቀመንበሩ ይህን ያሉት በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡
የአፍሪካ ገቢና የገንዘብ ምንጭ በሌሎች ሀገራት መወሰን የለበትም ያሉት ሊቀመንበሩ ፣ ከዚህ በፊት ሲያጋጥሙን የነበሩ እና አሁንም እያጋጠሙን የሚገኙ ችግሮችን በንግግር ለመፍታት በአንድነት ለመቆም ይህ ጉባኤ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ጉባኤው፣ ተለዋዋጭ የሆነውን የአለም ፖለቲካ የምንረዳበት እና የምንተነትንበት ነው በማለት አፍሪካዊያን ዝምታቸውን ሰብረው ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸውም ነው የገለጹት፡፡
ትክክለኛ እና ፈጠራ የታከለባት አፍሪካን በልማት ወደፊት ሊያሻግራት የሚችል የልማት አቅጣጫ በመቅረጽ ለስኬታማነቱ ሁሉም በንቃት ተሳታፊ መሆን እንደሚገባውም ነው ሊቀመንበሩ ያመላከቱት፡፡
አፍሪካዊያን፣ በአፍሪካዊነታቸው መኩራት እንደሚኖርባቸው ያሳሰቡት ሊቀመንበሩ በሚያወጧቸው ፖሊሲዎች እና በሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ዙሪያም እርስ በርስ በመግባባት፣ በአንድነትና በትብብር ሊቆሙ ይገባል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ሊቀመንበሩ በስራ ዘመናቸው ስለነበራቸው ቆይታ እና ከጎናቸው ሆነው ለአገዟቸው አካላት የተሰማቸውን ስሜት እና ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአስማረ መኮንን