
AMN-ህዳር 7/2017 ዓ.ም
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለተዋቂ አትሌቶችና ለነገ ተስፋ የሚጣልባቸው አትሌቶች የስኬታቸው መነሻ እንደሆነ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራች አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ገለፀ።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ1993 ዓ.ም የተጀመረና በየዓመቱ የሚከናወን የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ነው።
በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችን በማፍራት የራሱን ድርሻ ማበርከቱም ይታወቃል።
ዘንድሮም ”የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ህፃናት” በሚል መሪ ሀሳብ ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም ለ24ኛ ጊዜ 50 ሺህ ተሳታፊዎችን በማካተት ይከናወናል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራች አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋነኛ አስተዋፅኦ ለተዋቂ አትሌቶችና ለነገ ተስፋ የሚጣልባቸው አትሌቶች የስኬታቸው መነሻ መሆኑ ነው ብሏል።
በዚህ ውድድር ታዋቂ አትሌቶች ታይተው ዓለምአቀፍ ዝናን ያተረፉበትና የውድድር ዕድል ያላገኙ አትሌቶች የሚመለመሉበትና የተመለመሉበት እንደሆነም ተናግሯል።
ወድድሩም ከሩጫነቱ ባሻገር ለቱሪዝምና ለገፅታ ግንባታ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል ስለሚሳተፍበት ማኅበራዊ መስተጋብርን እንደሚያጠናክር ተናግሯል።
የዘንድሮው ውድድር ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበት 50ኛ ዓመት በማስመልክት፤ 50ሺህ ተሳታፊዎች የሚሳተፍበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በመጀመሪያው የታላቁ ሩጫ ውድድር ኃይሌ ገብረሥላሴ በወንዶች እና ብርሃኔ አደሬ በሴቶች አሸናፊ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ባለፈው ዓመት በተከናወነው የ23 ኛው ዙር የታላቁ ሩጫ ውድድር በወንዶች ቢንያም መሐሪ በሴቶች ደግሞ መልክናት ውዱ ማሸነፋቸው አይዘነጋም።
በአጠቃላይ በታላቁ ሩጫ ውድድር አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት፣ በሪሁ አረጋዊና አቤ ጋሻው ሶስት ሶስት ጊዜ ያሸነፉ ሲሆን በሴቶች ያለምዘርፍ የኋላው ሁለት ጊዜ ማሸነፏን ኢዜአ ዘግቧል።