አዲስ አበባ – አዲስም አበባም ናት። እንደ ከረመ ወይን እያደር እየጣፈጠች፣ እንደክት ልብስ እያማረች እና እንደፈንዲሻም በየዘመኑ እየፈካች ስለመሆኑ በርካቶች እየመሰከሩ ነው። ከሰሞኑም የደቡብ አፍሪካው ብሔራዊ የትምህርት አገልግሎት ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ቡሳኒ ንካዌኒ አዲስ አበባ- የራሷን ማንነት በራሷ መንገድ እየቀረጸች እና የአፍሪካ ብርሃን የመሆን ህልሟን እውን ለማድረግ እየተጋች ያለች ከተማ መሆኗን በደቡብ አፍሪካው ዴይሊ ማቭሪክ ጋዜጣ ላይ በሰጡት ሀሳብ ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገርም አዲስ አበባ እያስመዘገበች ባለው ሁለንተናዊ ለውጥ የተለያዩ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘቷ አይዘነጋም፡፡ ዓለም ባንክ እና አለም አቀፉ የአደጋ ቅነሳና ማገገሚያ ድርጅት እ.ኤ.አ በየካቲት 2015 በአዲስ አበባ መሰረተ ልማትና ተያያዥ ችግሮች ዙሪያ ባደረጉት ጥናት መሰረት ከተማዋ ታላቁን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤና ሌሎች መሰል ስብሰባዎችን የማስተናገድ ዕድሎች ቢኖሯትም የተሟላ የመሰረተ ልማት ግንባታ አለመኖር ለአብነትም ለከፍተኛ ዲፕሎማቶች፣ ለዓለም አቀፍ እንግዶች እና በትላልቅ ዝግጅቶች ላይ የሚሳተፉ ልዑካንን ለማስተናገድ የሚያስችል በቂና ጥራት ያላቸው ሆቴሎች አለመኖር፣ የትራፊክ መጨናነቅ፣ የከተማዋ የህዝብ ማመላለሻ መሠረተ ልማት ውስንነት፣ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ የህዝብ ማመላለሻ አማራጮች እጥረት፣ ያልዘመነ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት እና መሰል ችግሮች የመዲናዋ ፈተናዎች እንደነበሩ ተመላክቷል፡፡

የዘንድሮው ማለትም 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ግን የሚካሄደው ከበፊቱ በተሻለ ደረጃ መዲናዋ ምቹ መሰረተ ልማቶችን እያሟላች ባለበት ወቅት ነው፡፡ በተለይም በኮሪደር ልማቱ የተሰሩ መሰረተ ልማቶች የከተማዋን ገፅታ የቀየሩ በመሆናቸው ለጉባኤው ትልቅ ድምቀትን የሚፈጥር ስለመሆኑም በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉጌታ አስፋው ተናግረዋል፡፡
እንደ ዓለም ባንክ ጥናት ከሆነ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሉዓላዊነት ተምሳሌት መሆኗ አዲስ አበባ የአህጉሪቱ ዋና ማዕከል ትሆን ዘንድ ምቹ መደላድል ቢሆንም የአዲስ አበባ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ለብዙ ዓመታት የተጓተቱ ነበሩ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባ የከተማዋን መሠረተ ልማት ለማዘመን እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ከፍ ለማድረግ ያለመ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ጀምራለች። በከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ ውጤት እያስመዘገቡና ዓለም አቀፍ አድናቆትን እያስመዘገቡ ካሉ ተግባራት መካከል አንዱ ደግሞ ኮሪደር ልማት ነው፡፡
አዲስ አበባ ለዓመታት የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የህዝብ ትራንስፖርት ውስንነት እና የዘመናዊ አገልግሎቶች እጦት ትችት ሲሰነዘርባት ቆይቷል። የከተማዋ ጠባብ መንገዶች፣ የትራፊክ መጨናነቅ እና የዘመናዊ ኮንፈረንስ መገልገያዎች እጥረት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን ሲያስተናግድ ትልቅ እንቅፋት ነበሩ። ይሁን እንጂ መዲናዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍ ያለ ለውጥ እያስመዘገበች ይበልጥም ስሟን በሚመጥን መልኩ እየለማች ነው። በኮሪደር ልማቱና መሰል ተግባራት ከተማዋ የአፍሪካ ህብረት የመሳሰሉ ታላላቅ ጉባኤዎችን በከፍተኛ ብቃት ለማስተናገድ እንድትችል የሚያግዙ ልማቶችን እያከናወነች ስለመሆኑም መምህር ሙሉጌታ ገልፀዋል፡፡
እንደ የተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ (ዩ.ኤን.ሲ.ቲ.ኤ.ዲ 2016) መረጃ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ክስተቶችን በተደጋጋሚ የሚያስተናግዱ ሀገራት ብዙ ጊዜ የዓለምን ትኩረት ይስባሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የፖሊሲ ውይይቶች ላይ ተጽእኖ የማሳደር አቅምንም ያገኛሉ፡፡
እንዲህ አይነት ተመራጭነቶች ሀገራዊ አቅምን እና አንድነትን በማሳየት ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ትስስርን ሊያጎለብቱ ይችላሉ። ከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ስለሆነች የአፍሪካ ህብረትን የመሳሰሉ ጉባኤዎችን በብቃት ማስተናገድ ትችላለች። የተሳኩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን ማስተናገድ ደግሞ እንደ መንግስትም እንደ ዜጋም የኩራት ስሜትን ይፈጥራል ይላሉ መምህር ሙሉጌታ፡፡
አዲስ አበባ በኮሪደር ልማቱ ልዩ ገፅታን ተላብሳ ባለችበት ወቅት እንዲህ አይነት ታላላቅ ጉባኤዎች በመዲናዋ ሲከናወኑ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ይስባሉ፤ ይህም ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ እድገት ይሰጣል። ይህ የቱሪስት ፍልሰት ለተለያዩ ዘርፎች ማለትም መስተንግዶ፣ መጓጓዣ እና የተለያዩ የንግድ ማዕከላት ወይም ዘርፎች እንዲስፋፉ ያደርጋል።
አዲስ አበባ አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ማዕከል ሆነች ማለት እንደ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። የዓለምን ትኩረት የበለጠ ለመሳብ፣ የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለመፍጠር፣ በኢኮኖሚ የተሻለ ዕድገት ለማምጣት እና ይበልጥም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ጉልህ ሚና እንዲኖራት ያግዛል ይላሉ መምህሩ፡፡
አዲስ አበባ ላይ የተገኘ ሰው ሁሉንም አፍሪካ ሀገራት መዳሰስ ይችላል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ከሽብር አንፃር ስጋት የሌለባት ሀገር ናት። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ሁሌም የተሰጣትን የቤት ስራ ጥንቅቅ አድርጋ የተወጣች፣ ታላላቅ ጉባኤዎችን በስኬት ያጠናቀቀችና እንግዶቿን በበቂ መስተንግዶና ጥበቃ ያስተናገደች በመሆኗ እንደ አህጉርም ሆነ እንደ ዓለም አቀፍ አመኔታን ማትረፍ ችላለች፡፡
ይህ ደግሞ ከመንግስት የፀጥታና የደህንነት ጥበቃ ባሻገር የአዲስ አበባ ነዋሪ እንደ ሀገርም ኢትዮጵያዊያን እንግዳን እንደ ራስ አይቶ የማስተናገድ እና ለሰው ልጅ የሚሰጠው ክብር ከፍ ያለ መሆኑ ያስገኘው ዕድል እንደሆነም አክለዋል፡፡
በቅርቡ በመዲናዋ የሚከናወነው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ደግሞ ከተማዋ በብዙ መልኩ በውበት ላይ ውበትን በጨመረችበት፣ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ ምቹ መንገዶች፣ ሆቴሎችና መሰል መሰረተ ልማቶች በተሟላበት ወቅት በመሆኑ ለህብረቱ ጉባኤም ሆነ ለመዲናዋ ልዩ ገፅታን የሚፈጥር ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
ታላላቅ ጉባኤዎች በምቹ መሰረተ ልማቶች፣ መስተንግዶዎች እና በሰላም ሲጠናቀቁ የኢትዮጵያን ክብር እና ተመራጭነት በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ያደርጋል፡፡ በቀጣይም በሀገር ላይ ሙሉ እምነትን ሰጥተው እንዲመጡ ያደርጋል፡፡ አሁን እየተደረጉ ያሉ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ መድረኮችም ይህንን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ብዙሃን የሚጠቀሙበትን የእግረኛ መንገድ ማስፋትና ምቹ ማድረግ፣ የተሽከርካሪ መንገዶችን ማስፋት፣ መታደስ ያለባቸውን የአስፋልት መንገዶች ማደስ፣ አላስፈላጊ ናቸው የተባሉ የመንገድ ማካፈያዎችን አንስቶ መንገዱን ማስፋት፣ የመኪና ማቆሚያዎችን የመስራት፣ የመንገዶችን ዳር ማሳመር፣ የቴሌ፣ የመብራት ኬብሎችን በመሬት ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ፣ ዘመናዊ የንፁህ ውሃና ፍሳሽ ቆሻሻ መሄጃዎችን መስራት፣ የብስክሌት መንገድ መስራት፣ ፕላዛዎችን
መስራት ሌሎች ተያያዥ ስራዎች የሚያጠቃልል ነው። አብሮም ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች እየተሰሩ ነው። ይህም ለመዲናዋ አዲስ ገፅታን ያላበሰ እና ለአህጉራዊም ሆነ ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ትልቅ ድምቀትን የሚሰጥና ለመዲናዋም ዓለም አቀፍ ተመራጭነቷን የሚጨምር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን አስመልክቶ ከሆቴል ባለቤቶች እና ከዘርፉ አካላት ጋር በቅርቡ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት “የዘንድሮውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተሻለ ሁኔታ ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንገኛለን።” ብለዋል፡፡
በውይይቱም እንደተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትንና እንግዳ ተቀባይነታችንን አጉልተን በማሳየት በላቀ አገልግሎት ሰጪነት እንድናስተናግድ እንዲሁም ከተማዋን የቱሪዝምና የኮንፍራንስ ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን ስራ ይበልጥ በሚያጠናክር አግባብ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ትላልቅ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ በዘርፉ ላይ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር መግባባት ላይ ስለመደረሱም ገልፀዋል፡፡
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በቂ ዝግጅት አድርጋለች ብለዋል፡፡ ለጉባኤው ወደ መዲናዋ የሚመጡ መሪዎችንና ቀዳማዊት እመቤቶችን ለሚያስተናግዱ ዲፕሎማቶችና በጎ ፍቃደኛ የመሪ ባልደረባ ፕሮቶኮሎች ስልጠና መስጠት መጀመሩን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክታቸው የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት በልዩ ትኩረት ቀደም ብሎ ነው የተጀመረው።
ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫና የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ በሁሉም መስክ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቋንም አንስተዋል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመሪዎችና የቀዳማዊት እመቤቶች አስተናጋጅ ጀምሮ በዲፕሎማሲው መስክ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ወጣቶች ተለይተው ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የዘንድሮ 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የኮሚሽነሮች ምርጫ የሚካሄድበት እንደመሆኑ በርካታ እንግዶች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም፣ 46ኛው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ደግሞ ቀደም ብሎ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በገጸ ድሩ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡
በመለሰ ተሰጋ