AMN- የካቲት 23/2017 ዓ.ም
ታሪካችን የሚነግረን የሀገር ነፃነት እና ሰላም አደጋ ላይ ሲወድቅ በፅኑ የአንድነት መንፈስ በመቆም የሀገርን ሉአላዊነት የማስከበር አኩሪ ተግባርን ነው ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስገነዘቡ፡፡
በ129ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ባለንበት ዘመን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለመጉዳት ከሚመጣ ጠላት ጎን እቆማለሁ የሚሉ አንዳንድ ዜጎች መታየት መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡
ይህ በሀገራችን ታሪክ ያልነበረ የክሽፈት ደረጃ እንጂ የኢትዮጵያውያን ታሪክ አይደለም በማለትም ገልጸዋል፡፡
ወራሪው ኃይል ዓድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ለ40 ዓመታት በመዘጋጀት ሀገራችንን ከመውረሩ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል የሚያስችለውን በርካታ ሥራዎች መስራቱንም አንስተዋል፡፡
በዚህም በርካታ ዜጎች “ስልጣን ይሰጣችኋል” በሚል በማታለል በገንዘብ በመቅጠር በባንዳነት ከጎኑ እንዲሰለፉ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
ይህም ቅኝ ገዢዎች ጊዜያዊ ድል እንዲጎናፀፉ እና ለነፃነት በተደረገው ተጋድሎ ብዙ መስዋዕትነት እንዲከፈል አድርጓል ብለዋል፡፡
ዛሬም 129ኛውን የዓድዋ ድል እያከበርን ባለንበት ጊዜ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ተልዕኮ የተቀበሉ ሀገራችንን እያዳከሙ ናቸው በማለት ተናግረዋል፡፡
ዋናዎቹ ጠላቶቻችን እንወራችኋለን ሲሉ ከጠላት ጋር ኢትዮጵያን እንደሚወጉ ቃል እየገቡ እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡
ከጠላት ጋር በመሆን ሀገር በማዳከም መሰማራት የኢትዮጵያን ዝቅታ ለትውልድ ከማስተላለፍ ውጪ የኢትዮጵያን ከፍታ እንደማያረጋግጥም አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያን የገጠሟት የውጭ ወራሪዎችም ሆኑ የውስጥ ግጭቶች ጊዜያዊ መንገራገጮችን ከመፍጠር ባለፈ ኢትዮጵያን በዘላቂነት አንበርክከው እንደማያውቁም ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም “ወጀብ በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያ ትሸነፋለች፣ ትዳከማለች ብላችሁ ለጠላቶቻችን በማጎብደድ ክብራችሁን አትሽጡ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በታምራት ቢሻው