AMN_የካቲት 18/2017 ዓ.ም
ታይዋን ከባህር በታች ወደ ፔንዡ ደሴት የዘረጋችው የኮሙኒኬሽን ገመድ መቆረጡን ተከትሎ ከቻይና ጋር ግንኙነት አለው ያለችውን እቃ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ሥር አውላለች፡፡
የተቆረጠው የመገናኛ ወይም ኮሙኒኬሽን ገመድ ደሴቷ ከመላው ዓለም ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ወሳኝነት ያለው ነው ተብሏል፡፡
በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መግቢያ ላይ ሌላ በባሕር ውስጥ የተዘረጋ የመገናኛ ገመድ በቻይና መርከብ መቆረጡ ከተጠረጠረበት ጊዜ አንስቶ ታይዋን የባህር ኃይሏ የመገናኛ ገመድ ላይ ሊደርስ የሚችል ጥቃት እንዲከላከል ትዕዛዝ ሰጥታ ነበር፡፡
አካባቢውን በአንክሮ ሲከታተል የቆየው የድንበር ጠባቂ ኃይልም ከቻይና ጋር ግንኙነት እንዳለው የጠረጠረውን እቃ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ ከመርከቡ ጋር 8 የቻይና ዜግነት ያላቸው ሰዎች መኖራቸውንም አመላክቷል፡፡
መርከቡ የባለቤት ሀገርን ሳይሆን የሌላ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ለቻይና በእጅ አዙር እያገለገለ ሊሆን ይችላል በሚል አስጠርጥሮታል፡፡
የታይዋን ዲጂታል ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ጉዳት የደረሰበት ገመድ በሌላ በመተካቱ ታይዋን ፔንዡን ጨምሮ ከተቀሩት ደሴቶች ጋር ያላት ግንኙንት አልተቋረጠም፡፡
በታይዋን ተመሳሳይ የባህር ውስጥ የመገናኛ ገመድ መቆረጥ አደጋ ሲደርስ ይህ ለ5ኛ ጊዜ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ቻይና በጉዳዩ ላይ እስከ አሁን ምንም ያለችው ነገር አለመኖሩን ሬውተርስ ነው የዘገበው፡፡