“ትምህርት ለትውልድ” ምን ውጤት አመጣ?

You are currently viewing “ትምህርት ለትውልድ” ምን ውጤት አመጣ?

ተማሪ ሱራፌል መንግስቱ ይባላል። የበሻሌ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ የትምህርት ቤታቸው የቀደመ እና አሁን ላይ ያለው ሁኔታ በብዙ መመዘኛ የተለያየ መሆኑን ይናገራል፡፡ በትምህርት ቤቱ ስለታየው ለውጥ፣ የልዩነታቸው ምክንያት፣ ምንነት እና በንፅፅር ምን እንደሚመስሉ ለመግለፅ አልተቸገረም፡፡

ተማሪው እንደገለፀው፤ ትምህርት ቤቱ ቀደም ባሉት ዓመታት (የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር ከመተግበሩ በፊት) በቂ የመማሪያ ክፍሎች አልነበሩትም፡፡ ዘመኑ የሚጠይቀውን የኮምፒዩተር ዕውቀትና ክህሎት በመሰረታዊነት ለመማርና ለማወቅ የሚያስችሉ ግብዓቶች የተሟሉለት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (የአይሲቲ) ማዕከል እንዲሁም ቤተ ሙከራ አልነበሩትም፡፡  በግብዓት የተደራጀ ቤተ መጽሐፍ ማግኘት የማይታሰብ ነበር፡፡  በዚህም ለፈተና በቂ ዝግጅት እንዳያደርጉ እንቅፋት ይፈጥርባቸው ነበር፡፡  ተማሪዎች የአካል ብቃት የሚያደርጉበት፣ ከቀለም ትምህርታቸው በተጓዳኝ አካላቸውንና አዕምሯቸውን ዘና የሚያደርጉባቸው የመጫወቻ ሜዳዎችም አልነበሩም፡፡

ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ በትምህርት ቤቱ መማሩን የሚገልጸው ተማሪ ሱራፌል፤ የትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ምቹ አልነበረም፡፡ በተለይም መስከረም አካባቢ ትምህርት ሲጀመር ዝናብ ስለሚዘንብ ተማሪዎችና መምህራን ለመንቀሳቀስ ጭቃ ያስቸግራቸው ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ብዙ ነገሮች ተሟልተዋል፡፡ በችግርነት ይነሱ የነበሩ ተቀርፈዋል፡፡ ለትምህርት አቀባበላቸውም ሆነ ለውጤታማነታቸው አቅም የሚፈጥር መልካም ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለዚህ ደግሞ፤ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለመማር ማስተማር ሂደቱ አጋዥ እና  አስፈላጊ ግብአቶች መሟላታቸው፣ ቅጥር ግቢው ፅዱ፣ ምቹና ማራኪ መሆኑን በማሳያነት ያነሳል። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት፣ ጨዋታዎችን የሚያከናውኑበት ሜዳ ተሠርቶ ለአገልግሎት መብቃቱ፣ የቤተ መጻሕፍቱና ቤተ ሙከራ በተገቢ ሁኔታ መደራጀቱ እና በግብዓት መሟላቱ  በንድፈ ሀሳብ የሚማሩትን ትምህርት የበለጠ በተግባር አይተው እንዲረዱት በማድረግ የተሻለ እውቀት ለመጨበጥ አስችሎታል። ይህም በትምህርቱ ውጤታማ እንዲሆን እንዳደረገውና በዚህም ደስተኛ እንደሆነ ነው የተናገረው፡፡   

የበሻሌ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሂሩት ሰይፉም የተማሪ ሱራፌልን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ ትምህርት ቤቱን የሚያውቁት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነና ግቢውም በበጋ አቧራው፣ በክረምት ደግሞ ጭቃው ለመግባትና ለመውጣት ያስቸግር እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ “ተማሪው በክረምት በጭቃ ተለውሶ ነበር ክፍል ውስጥ ለመማር የሚገባው፡፡ በበጋም በአቧራው ምክንያት ለጉንፋንና ተያያዥ በሽታዎች ይጋለጡ ነበር፡፡ በተጨማሪም ተማሪውና መምህሩ በአንድ ህንጻ ብቻ በተጨናነቀ ሁኔታ የመማር ማስተማር ሂደቱን ያካሂዱ ነበር” በማለትም የትምህርት ቤቱን የቀደመ ገፅታ ለማስታወስ ይሞክራሉ፡፡

በተማሪ ሱራፌል የተገለፀው እና የትምህርት ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሆኑት ወይዘሮ ሂሩት የተደገፈው የበሻሌ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመማር ማስተማሩ ሂደት አመቺ ያልሆነ ገፅታ እና ሁኔታ እንዲለወጥ ጉልህ ሚና የተጫወተው ከጥቂት ዓመታት በፊት ተግባራዊ የተደረገው “የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ” እንደሆነ ይመሰክራሉ፡፡ ለመጣው ሁለንተናዊ ለውጥ የማህበረሰቡና ባለሀብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዋን ፕላኔት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ባለቤት በተገኘ ድጋፍ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ያለፈረቃ ማስተማር የሚያስችል ክፍል መገንባት መቻሉንም በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

የወላጅ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ አክለው እንዳስረዱት፤ መጽሐፍት ቤቱን በግብአት በማሟላት ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በማንበብ እንዲያሳልፉ አስችሏቸዋል፡፡ በትምህርታቸው ውጤታማ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታም ፈጥሮላቸዋል፡፡ የመምህራንንም ተነሳሽነት ከፍ አድርጎታል፡፡ መምህራን ከመደበኛ የትምህርት ቀናት በተጨማሪ፤ ለተማሪዎች ውጤታማነት ቅዳሜ እና እሁድን ያስተምራሉ፡፡ እሳቸውን ጨምሮ  የትምህርት ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ አመራሮች እና አባላት በጠዋት ወደ ትምህርት ቤት በመምጣት የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዴት እየተካሄደ እንደሆነ፣ የተማሪዎችን ውጤታማነት ክትትል የሚያደርጉበትን ኃላፊነት እንዲወጡ፤ ይህንንም ልምድ አድርገው እንዲያስቀጥሉ አድርጓቸዋል፡፡

የትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አበበ ሽፈራው በንቅናቄው አማካኝነት በትምህርት ቤቱ   ስለተሠሩ ሥራዎች እና ስለተገኘው መሰረታዊ ውጤት ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እሳቸው እንደገለጹት፤ ንቅናቄው ከመተግበሩ በፊት ትምህርት ቤቱ የነበረበት ሁኔታ ለመማር ማስተማር ሥራ እጅግ የማይመች ነበር፡፡ የመማር ማስተማሩ ተግባር እንዲሁም የአስተዳደር ሥራው የሚከናወነው ባለ አራት ወለል አንድ ሕንፃ ላይ ነበር፡፡ ሁሉ ነገር የተጨናነቀና የማይመች ነበር፡፡  በአንድ ክፍል ውስጥ ቁጥራቸው ከ80 እስከ 90 የሚደርሱ ተማሪዎች ይማሩ እንደ ነበር አስታውሰው ይህም በትምህርት ጥራቱ እና በመማር ማስተማሩ ሂደት  ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ክረምት ላይ በተጀመረው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ትምህርት ቤቱን አስገራሚ ወደሆነ ለውጥ የሚያስገቡ ተግባራት መከናወን መጀመራቸውን የሚያስታውሱት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር፤ በወቅቱ ከተሠሩት ሥራዎች መካከልም በመንግስት 30 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት አንድ ባለ አራት ፎቅ ህንጻ፣ በባለሀብቶችና በማህበረሰቡ የጋራ ተሳትፎ ደግሞ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ የሚያገለግሉ አራት የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጽሐፍት፣ ቤተ ሙከራና የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይ ሲ ቲ)፣ ላቦራቶሪ፣ ለተማሪዎች የምገባ አገልግሎት የሚውል ዘመናዊ ማብሰያ እና መመገቢያ አዳራሽ እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ እና መጫወቻ ሜዳ ማስተካከል፣ ምድረ ግቢ ማስዋብና አረንጓዴ የማድረግ ሥራዎች በስፋት ተከናውነዋል፡፡ ለዚህ ሰፊ እና ወሳኝ ሥራ በአጠቃላይ ከአንድ መቶ ሚሊየን ብር በላይ የሆነ መዋእለ ነዋይ ወጪ መሆኑን በመጥቀስ፤ በንቅናቄ በተሠራው ሥራ የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሳለጠ እንዲሆን መደረጉን አብራርተዋል፡፡

እንደ ርእሰ መምህሩ ገለጻ፤ በትምህርት ቤቱ  በንቅናቄው የመጣውን ውጤት ማየት የተጀመረው በ2016 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ሲሆን፤ በዚህም የተማሪ የማለፍ ምጣኔ ተሻሽሏል፡፡ በመሆኑም  በትምህርት ቤቱ በ2016 የትምህርት ዘመን ፈተና ከወሰዱ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት ከተማ አቀፍ ፈተና ውጤት ማለፊያን አስመዝግበዋል። በተመሳሳይ፤  የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል  89 በመቶዎቹ ወደ ቀጣዩ ክፍል ማለፍ ችለዋል፡፡ በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም ከባለፈው የተሻለ ውጤት ትምህርት ቤቱ እንደሚያስመዘግብና ለዚህም አስፈላጊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ንቅናቄው ያስገኘውን ውጤት በሌላ ትምህርት ቤት ተገኝተን ያነጋገርናቸው ባለድርሻ አካላትም ይጋሩታል፡፡ የእድገት ጮራ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሜሮን በፍቃዱ፤ ከዚህ ቀደም ትምህርት ቤታቸው ምቹ እንዳልነበረ በማስታወስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከቅጥር ግቢው ጀምሮ ከፍተኛ መሻሻል እና ለውጥ እንዳመጣ ትመሰክራለች። እንደ እርሷ ዕይታ፤ የትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ የተመቸ እና በአረንጓዴ ዕጽዋት የለማ ሆኗል፡፡ ይህም ትምህርት ቤቱን ሳቢ እንዲሆንና ነፋሻማ አየር እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን (አይሲቲ) ጨምሮ የተለያዩ ቤተ ሙከራዎች እና ቤተ መጽሐፍት በተደራጀ መልኩ ተሟልቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

“ቀደም ሲል የነበረው  መጽሐፍት ቤት በቂ መጽሐፍት የሌለው፣ ጽዳቱ ያልተጠበቀና ጸጥታ ያልነበረው ከመሆኑ የተነሳ ለተማሪው ብዙም ጥቅም አይሰጥም ነበር” የምትለው ተማሪ ሜሮን አሁን ላይ ግን የተለያዩ አጋዥ መጻሕፍት ተሟልቶለታል፤ ከጸጥታው ጋር የነበረውን ችግር ለመፍታት ካሜራ ተገጥሞለታል፡፡ ይህም በትምህርታቸው ውጤታማ ለመሆን የሚያስችላቸውን በቂ ዝግጅት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነግራናለች ፡፡

በትምህርት ቤቱ የ11ኛ ክፍል ተማሪው አዶናይ ጣዕመ በበኩሉ፤ ትምህርት ቤቱ ከቀደመው ገጽታው ጋር ሲነጻጸር በብዙ

መልኩ መለወጡን ያስረዳል፡፡ ተማሪው እንደተናገረው፤ ትምህርት ቤታቸው በሠራው ሰፊ ሥራ የእግርና ቅርጫት ኳስን ጨምሮ ተማሪዎች አዕምሯቸውን ዘና የሚያደርጉበት እንዲሁም ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት የተለያዩ መጫዎቻዎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡ በጥሩ ሁኔታ ተገንብተውና ግብዓት ተሟልቶላቸው ለአገልግሎት የበቁት የተለያዩ ቤተ ሙከራዎች፤ በንድፈ ሃሳብ ላይ ብቻ ይሰጣቸው የነበረውን ትምህርት በተግባር ተኮር ሙከራ እንዲታገዝ የሚያደርግ ዕድልን ፈጥሮላቸዋል፡፡ እሱ እና የክፍል አቻዎቹ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ በነበራቸው የትምህርት ሕይወት በቤተ ሙከራ መታገዝ የነበረባቸውን የትምህርት ዓይነቶች በንድፈ ሀሳብ ብቻ ተምረው እንዲያልፉ አስገድዷቸው የነበረው ጉድለት፤ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በተሠሩት የተለያዩ ቤተ ሙከራዎች የተማሩትን በተግባር ለማወቅ ሰፊ እድል የፈጠረና ምሉዕ የሆነ እውቀት እንዳስጨበጣቸው ይናገራል፡፡

በትምህርት ቤቱ የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል የቤተ ሙከራ ቴክኒሺያን አቶ ዘውዱ ሀይሉ ስለጉዳዩ እንዳብራሩት፤ ቤተ ሙከራው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሥራውን በተሟላ ሁኔታ መስጠት ጀምሯል፡፡ ይህም የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን በማድረግ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

“‘የሰማሁትን ልረሳ፤ ያየሁትን ላስታውስ እችላለሁ፡፡ የሰራሁትን ግን አውቀዋለሁ’ የሚባል አባባል አለ” የሚሉት አቶ ዘውዱ፤ ቤተ ሙከራው ተማሪዎች በተግባር የሰሩትን በሚገባ ለማወቅና ለማስታወስ እገዛ ያደርግላቸዋልም ነው ያሉት፡፡ በተለይም ቤተ ሙከራው አዲስ ከመሆኑ የተነሳ ተማሪዎች በከፍተኛ ተነሳሽነትና ፍላጎት ለማወቅ ስለሚጥሩ ውጤታማነታቸውን በሚገባ አሻሽሎታል፡፡    

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ዘነበ አደፍርስ፤ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የተሠሩ  ሥራዎችን በተመለከተ ለዝግጅት ክፍሉ እንደገለጹት፤ በንቅናቄው የቁሳቁስ ድጋፉን ሳይጨምር ከህብረተሰቡ የ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ደግሞ 300 ሺህ ብር ድጋፍ ተገኝቷል፤ በዚህም አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተሰርተውበታል፡፡ ከተሠሩት ሥራዎች መካከል፤  አንደኛው ባለሁለት ፎቅ ህንጻ ግንባታ የተከናወነ ሲሆን በዚሁ ህንጻ ሁለት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ቤተ ሙከራ፣ ሦስት ቤተ ሙከራዎች፣ አንድ ቤተ መጽሐፍት እና ሌሎች ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት እና ለመማር ማስተማሩ ሥራ ውጤታማነት ማዋል ተችሏል፡፡

ርዕሰ መምህሩ አክለውም፤  በግቢ ማስዋብ 500 ካሬ የሚሆነውን የትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ቴራዞ ተነጥፏል፡፡ የትምህርት ቤቱን የውስጥ ለውስጥ መንገድም ኮብል ስቶን የማንጠፍ ስራ ተሰርቷል፡፡ እንዲሁም የእግር ኳስ ሜዳም ተሰርቷል፡፡  ከዚህ በተጨማሪም ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመከተል መምህራን በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማሩ ሂደቱን ለመከታተል የሚያግዝ የደህንነት ካሜራዎች ተገጥመዋል። ይህም ተማሪዎች ያለምንም ስጋት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለጻ፣ በንቅናቄው የተሰሩ ስራዎች የተማሪዎችን ውጤታማነት አሻሽሏል፡፡ የዘንድሮው የተማሪ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ አሳይቷል።  የ2016 ከ2015 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የ12ኛ ክፍል የማለፍ ምጣኔ 50 በመቶ የጨመረበት እንዲሁም ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል የተማሪዎች  ከክፍል ወደ ክፍል የማለፍ ምጣኔ ከ87 በመቶ ወደ 92 በመቶ ከፍ ያለበት እንደሆነ ለማየት ተችሏል። ንቅናቄው በተማሪ ሥነ ምግባር ላይም መሻሻል እንዲመጣ አድርጓል። ባለፉት ዓመታት በአጥር ዘለው ይወጡ የነበሩና ክፍል ውስጥ ገብተው መማር የማይችሉ ሥነ ምግባራቸው የተበላሸ ተማሪዎች እንደነበሩና አሁን ላይ በተቃራኒው የመማር ፍላጎታቸው ያደገ ተማሪዎችን በተጨባጭ መፍጠር ተችሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት ትምህርት ቤቱ ደረጃ 2 ላይ የነበረ ሲሆን በቀጣይ በሚኖረው ግምገማ የተሻለ ደረጃ ላይ ሊቀመጥ እንደሚችል ነው  ርዕሰ መምህሩ የጠቀሱት፡፡

የዝግጅት ክፍላችን ከላይ በተጠቀሱት ትምህርት ቤቶች ምልከታ አደረገ እንጂ ንቅናቄው በመዲናዋ በሚገኙ  የመንግስት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ሪፖርት በምክር ቤት ተገኝተው ባቀረቡበት ወቅት እንዳብራሩት፤ ባለፉት ስድስት ወራት በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በገንዘብ 3 ቢሊዮን 841 ሚሊዮን 682 ሺህ 948 ብር፣ በዓይነት 137 ሚሊዮን 566 ሺህ 563 ብር፣ በጉልበት 19 ሚሊዮን 800 ሺህ 640 ብር እና በእውቀት 26 ሚሊዮን 380 ሺህ 54 ብር በድምሩ ብር 4 ቢሊዮን 25 ሚሊዮን 430 ሺህ 206 ብር በላይ በመሰብሰብ የትምህርት ግብዓትን የማሟላት ስራ ተሰርቷል።

ከትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ጋር በተያያዘ ከአዲስ ሚዲያ ኔትውርክ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) እንዳስረዱት፤ የትምህርትን ውጤታማነት ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች በሚያደርጓቸው ቆይታዎች ብቻ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ልጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከወላጆቻቸው ጋር ስለሆነ፤ ወላጆች በትምህርት ላይ የሚያደርጉት ተሳቴፎ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ንቅናቄው መሰረት ጥሏል፡፡ ይህንን በገንዘብ የማይተመን ወሳኝ አስተዋፅኦ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡ ልጆች የተሰመረላቸውን መስመር ተከትለው ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ወላጅ ክትትል የሚያደርግበትንም መደላድል ንቅናቄው ጥሏል፡፡ በንቅናቄው የትምህርት ቤቶች አዕምሯዊም፣ ውስጣዊም አቅም አድጓል። አዳዲስ ክፍሎችም ተገንብተዋል፡፡

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review