ትውልድ ገንቢው አሻራ

You are currently viewing ትውልድ ገንቢው አሻራ

በዓድዋ ድል መታሰቢያ የህጻናት ሙዚየም ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት እየተሰራ ነው

               የመታሰቢያው ዋና ዳይሬክተር አቶ ግሩም ግርማ                      

 “የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነፃነት፣

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት።

ምሥጋና ለእነርሱ ለዓድዋ ጀግኖች፣

ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች፡፡”… እያለች አርቲስት እጅጋየሁ ሽባበው (ጂጂ) ‘ዓድዋ’ በተሰኘው ዘመን አይሽሬ ስራዋ ጥልቅ በሆነ ሀሳብ የድሉን ዋጋ፣ ታላቅነቱን፣ ለሰው ልጅ ያለውን ትርጉም ትገልጻለች፡፡

አዎ! አያት፣ ቅደመ አያቶቻችን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮማ ተነስቶ ቀይ ባህርን አቋርጦ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የመጣው ሀይል በብርቱ ክንዳቸው ድባቅ በመምታት የኢትዮጵያ ነፃነትና ሉዓላዊነት ተጠብቆ እንዲቀጥል የከፈሉት መስዋዕትነት ዋጋው ከፍ ያለ ነው፡፡ ድሉ ከሀገር አልፎ ለአፍሪካና በመላው ዓለም ለሚኖረው ጥቁርና ጭቁን ህዝብ የነፃነት ችቦን አቀጣጥሏል፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ የነፃነት፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ምልክት (Symbol) ነው፡፡ ተክለጻድቅ መኩሪያ ‘ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ’ በሚለው መጻሐፋቸው ላይ  እንዳሰፈሩት “… ከንጉሱ ጋር ሆነው የድል አድራጊነቱን ዕድል የተካፈሉትን መሳፍንት ማመስገን ይገባል። ምክንያቱም ከእነዚህ አንዱ ዳግማዊ ምኒልክን እንደሸዋ ንጉስና እንደባዕድ ቆጥረው የራሳቸውን ምኞት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለመፈፀም በመሞከር ተለይተው ቢሆን ኖሮ፣  ‘እንሸፍት ንጉሱን ለምን’ በማለት የውስጥ ግጭት ተነስቶ ቢሆን ኖሮ የኢጣሊያን ጦር ምን ያህል ይጠቅመው እንደነበር ግልፅ ነው።

የኢጣሊያ የጦርና የፖለቲካ መሪዎች ውስጥ ለውስጥ እየተላላኩ ጆሯቸውን ከፍተው የጠበቁት ይህንን ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ አንድነት፣ የመኳንንትና የመሳፍንቱ ህብረት፣ የጦር ሰራዊቱ ታማኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የጠበቀ ነበር” ሲሉ ለድሉ መገኘት የኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆም የነበረውን ሚና አመላክተዋል፡፡

ይህንን ታላቅ ድል በሚመጥነው መልኩ ለመዘከር ይቻል ዘንድ ከ128 ዓመታት በኋላ፣ በታሪካዊው ፒያሳ ላይ በኪነ ጥበባዊ መንገድ የተገነቡ ኪነ ህንጻዎችን ያቀፈ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተገንብቶ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለህዝብ ክፍት ሆኗል፡፡

መታሰቢያው የኢትዮጵያውያን፣ አፍሪካውያንና ከመላው ዓለም የመጡ ዜጎች የጉብኝት መዳረሻ ሆኗል፡፡ ጉብኝት ሲያደርጉ ካገኘናቸው መካከል ከወሊሶ የመጣው ወጣት ዘነበ በቸሬ አንዱ ነው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገብቶ ታሪክ እንደተማረ የሚናገረው ወጣቱ፣ የዓድዋ ድል የታሪክ መጻሕፍትን በማንበብና ሰዎች ከሚናገሩት በመስማት ያውቀው እንደነበር ይናገራል፡፡

“መታሰቢያውን ከጎበኘሁ በኋላ የተለየ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ ጀግኖች እናቶቻችንና አባቶቻችን የሀገርን ነፃነት ለማስጠበቅ የከፈሉት ዋጋ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ተረድቼዋለሁ፡፡ በዚያን ወቅት ምን ዓይነት የጦር መሳሪያ ታጥቀው፣ በእነዚያ ፈታኝ ተራራዎች ወጥተው ወርደው፤ እንዴት ተዋግተው አሸነፉ እያልኩ በምናቤ እየሳልኩ ነበር ስመለከት የነበረው፡፡ በመጽሐፍት ከማውቀው በላይ ብዙ ቁም ነገር አግኝቼበታለሁ፤ ተደስቻለሁ፡፡” ሲል በፈገግታ ስሜቱን አጋርቶናል፡፡

ሌላው መታሰቢያውን ሲትጎበኝ ያገኘናት የሳውዝ ዌስት አካዳሚ የአስረኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው አሜን ዘውዱ፣ የዓድዋ ጦርነት አባቶቻችንና እናቶቻች ለእኛ ነፃነት ሲሉ ኢትዮጵያን ሊወር ከመጣው ሀይል ጋር ተዋግተው ድል ያደረጉበት ነው። መታሰቢያው ከጠበቅኩት በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የተዋጉባቸውን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ አባቶቻችን የከፈሉትን መስዋዕትነት፣ በጦርነት ሴቶች የነበራቸውን አስተዋፅኦ ተመልክቻለሁ ብላለች፡፡

በሀገራችን ታሪክ መኩራት ይኖርብናል፤ አባቶቻችንና እናቶቻችን ለከፈሉት መስዋዕትነት ክብርና ምስጋና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በወቅቱ በአንድነትና በፍቅር ሆነው የሀገርን ነፃነት እንዳስጠበቁ ሁሉ፤ እኛም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በፍቅር መስራት አለብን ስትልም መልእክቷን አስተላልፋለች፡፡

በአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የሳይንስ መምህር ባሻ አሰፋ፤ ህፃናት የወደፊት ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንደመሆናቸው ቀደምት አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው የሰሩትን አኩሪ ታሪክ እንዲያውቁ ማድረግ እነሱም ዛሬ ሀገርን ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አሻራ እንዲያኖሩ ያግዛል፡፡ መታሰቢያው ትውልዱ የሀገር ፍቅርን ዋጋ ተረድቶ የተሻለ እንዲሰራ የሚያነሳሳ ትልቅ ትምህርት ቤት እንደሆነም ተናግሯል፡፡

በመታሰቢያው ህፃናትና ወጣት ተማሪዎች እየተዝናኑ፣ በተለየ መገረም፣ ደስታ በሚነበብት ፊት የአባቶቻቸውንና እናቶቻቸውን ታሪክ ሲመለከቱ፣ ያልገባቸውን ሲጠይቁ፣ በሙዚየሙ ውስጥ ያሉ ቁሳቀሶች፣ ጽሑፎችን በአትኩሮት ሲመለከቱ አይተናል፡፡

መታሰቢያው ለትውልዱ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?

የዓድዋ ድል በየዓመቱ የሚዘከር ቢሆንም ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመዘከር መታሰቢያ መገንባቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ታከለ መርዕድ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል። በመታሰቢያው የዓድዋ ድልን የሚመለከቱ፣ ኹነቱን የሚገልፁ የተለያዩ ቁሳቁሶችና መረጃዎች ይሰባሰቡበታል። በዚያን ወቅት ኢትዮጵያውያን እና ወራሪው ሰራዊት የነበራቸው አሰላለፍ፣ የጦርነቱ ሁኔታና መሰል ጉዳዮችን ሰዎች እያዩ ያደንቃሉ፡፡ በመታሰቢያው በሚኖረው ቤተ መጽሐፍት ሰዎች እያነበቡ ድሉን ይረዳሉ፡፡ ትውልዱ ሀሳቡን ሰብስቦ ለሀገሩ እንዲቆምና ወደ አንድነት እንዲመጣ ያግዛል ይላሉ፡፡

የታሪክ ተመራማሪው ዲያቆን ተረፈ ወርቁ እንዲሁ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ ሳይሉ በአንድነት በመተባበር ያስመዘገቡትን ታላቁንና ታሪካዊውን የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን የአንድነታችን ሕያው ምልክትና የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭ ነው፡፡

በዓድዋ የኢትዮጵያውያን የነፃነት ተጋድሎና ድል አፍሪካን፣ መላው ጥቁር ሕዝቦችንና በአጠቃላይ ነፃነታቸውን የሚናፍቁ የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድነት ያስተሳሰረ ነው፡፡ ዛሬ በኩራት የምንተነፍሰው የነፃነት አየር፣ በዓለም ፊት ደረታችንን ነፍተን የምንናገርለት የአባቶቻችንና እናቶቻችን የነፃነት ታሪክ ተጋድሎ፣ በደም የከበረ፣ በዋጋ የማይተመን የብዙዎች ክቡርና ውድ ሕይወት የተከፈለበት ነው ሲሉ የድሉን ዋጋ አስረድተዋል፡፡

የታሪክ ተመራማሪው እንደሚያስረዱት፣ የዓድዋ ድልን በታላቅ ክብር የሚዘክረው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለኢትዮጵያና ለመላው አፍሪካና ጥቁር ህዝቦች የኩራት፣ የአሸናፊነትና ሰው የመሆን ክብር ሕያው አሻራ ነው፡፡ መታሰቢያው ትውልዱ በዓይኖቹ እያየ፤ በእጆቹ እየዳሰሰ ስለ ነጻነት ክብርና ስለ አፍሪካውያን የነጻነት ተጋድሎ በተግባር የሚማርበት በመሆኑ ለትውልድ ግንባታ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡

መታሰቢያው የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም በተመረቀበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፤ “የዓድዋ ድል የእውነተኛ፣ የጠንካራና የአንድነት ውጤት መሆኑን ትውልድ ይማርበታል፡፡ መታሰቢያው ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ የሚያስተሳስር ድልድይ ነው፤ መላው ኢትዮጵያውያን በአንድ ቋንቋ እንዲግባቡ የሚያደርግ የመጪው ትውልድ ስጦታችን ነው” ሲሉ ነው የመታሰቢያውን ፋይዳ የገለፁት፡፡ 

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግሩም ግርማ በበኩላቸው፣ ታላቁ የዓድዋ ድል በልኩ የሚዘከርበት ታላቅ መታሰቢያ መገንባቱ ትውልዱ የሀገሩን የቀደመ አኩሪ ታሪክና የተከፈለውን ዋጋ እንዲረዳ፣ ለወደፊትም ምን መስራት እንዳለበት መነሳሳት እንዲፈጠር  በማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡

ዓድዋን በዜና ዘገባና ዓመቱን ጠብቆ መታሰቢያው አካባቢ ከሚደረገው ዝግጅት ባሻገር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደራሱ ታሪክ ከልጅነቱ ጀምሮ በልቡ እንዲሰርፅበት መስራት ይገባል፡፡ በዚያን ጊዜ ሀገራችን ምን ሁኔታ ላይ ነበረች? እናቶቻችንና አባቶቻችን ደመወዝ ሳይከፈላቸው፣ ስልጠና ሳያገኙ፣ አርሶ አደሮች ሞፈርና ቀንበራቸውን ሰቅለው፣ ቤተሰባቸውን ጥለው ከጫፍ እስከ ጫፍ ሀገራቸውን ለማዳን የተነሱት ለምንድን ነው? የሚለውን የአሁኑና የወደፊቱ ትውልድ በደንብ ሊረዳ ይገባል፡፡

ከዚህ አኳያ መታሰቢያው የዓድዋን ታሪክ ይዞ በተሟላ መልኩ ለማስተማሪያነት፣ ለጥናትና ምርምር አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ግሩም ያነሳሉ፡፡

“የዓድዋ ድል ከአሁኑ ትውልድ በፊት የተሰራ ድል ነው፡፡ እኛ ሰምተን የተረዳነው ነገር አለ፡፡ የሚመጣው ትውልድ ደግሞ ከዚህም በላይ በሚመጥነው ልክ ከልጅነቱ ጀምሮ ድሉ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ምን እንደሆነ በአግባቡ እንዲረዳ የህጻናት ሙዚየም ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት እየተሰራ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ህፃናት ዓድዋን በአእምሯቸው ሊስሉትና ሊረዱት በሚችል መልኩ ታሪኩን እንዲያውቁት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ የህፃናት ሙዚየም ለማደራጀት በተያዘው ዓመት ጥናት ይጀመራል፡፡ ይህም እንደ ሀገር እንዲመጣ የሚፈለገውን ገዥ ትርክት በመፍጠር ረገድ ትልቅ  አስተዋፅኦ ይኖረዋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር ቤተ መጻሕፍት የማደራጀት ስራ እንደሚከናወን አቶ ግሩም ጠቁመዋል፡፡ የዓድዋ ጦርነት መነሻ፣ ድሉን፣ በወቅቱ የነበሩ ሁነቶችን የሚገልፁ ማናቸውም መጽሐፍትና የህትመት ውጤቶች መሰብሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ለመጪው ትውልድ ታሪኩን በቃል ከመንገርና ስዕሎችን ከማሳየት ባሻገር በተለያዩ ሰዎች የተፃፉ ስራዎችን በማሰባሰብ ማንበብ የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ዓድዋን በትውልዱ ላይ ለማስረፅ ጥናትና ምርምሮች እየተደረጉ ሴሚናር እየተዘጋጀ እንዲቀርብ በማድረግ ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ ማድረግ እንደሚገባ ታከለ (ዶ/ር) ያነሳሉ፡፡ በየዓመቱ በዓሉን ከመዘከር ባለፈ ሀገራችንን ወደፊት ለማሻገር ምን ማድረግ አለብን? የሚለው ላይ በመወያየት በትውልዱ ልብ ውስጥ እንዲሰርፅ መስራት ይገባል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review