ንጋት ኮርፖሬት 1.8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለጸ

You are currently viewing ንጋት ኮርፖሬት 1.8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለጸ

AMN – መጋቢት 8/2017 ዓ.ም

በአማራ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የልማት ድርጅቶችን ያቀፈው ንጋት ኮርፖሬት እኤአ በ2024 በጀት ዓመት 1.8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ትርፍ በማስመዝገብ የዘላቂ ልማት መሠረት እየሆነ መምጣቱን ገልጿል።

የንጋት ኮርፖሬት፣ ኩባንያዎች የ2024 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸምን አስመልክቶ አመታዊ ዕውቅናና ሽልማት መርሃ ግብር አካሄዷል።

ኩባንያዎቹ የአማራ ክልልን ኢንዱስትሪያላይዜሽንና ግብርናን እንዲያግዙ እየሠራ እንደሆነ ነው ኮርፖሬቱ የገለጸው።

በ2024 የበጀት ዓመት ጠቅላላ የምርት ሽያጭ ገቢው 10.3 ቢሊዮን ብር እንደሆነ የገለጹት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የንጋት ኮርፖሬት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ስዩም መኮንን፣ በዚሁ በጀት ዓመት ያገኘው የተጣራ ትርፍ ከ1 ቢሊዮን 792 ሚሊዮን 18 ሺህ ብር በላይ መሆኑንም በዕውቅናና ሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ ይፋ አድርገዋል።

በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው ትርፍም በንጋት ኮርፖሬት ታሪክ ትልቁ የትርፍ መጠን የተመዘገበበት ስለመሆኑም ነው አቶ ስዩም መኮንን ያስታወቁት።

ንጋት ኮርፖሬት በማህበራዊ ልማትና ኃላፊነት ረገድም ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 71.7 ሚሊዮን ብር በመመደብ ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ ለህክምና መሳሪያዎች፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እና በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ሰብአዊ ድጋፍ ማበርከቱንም አስታውቀዋል።

ኮርፖሬቱ፣ ለ9 ሺ 494 ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል በመፍጠር በአማራ ክልል ደረጃ ከክልሉ መንግስት በመቀጠል በርካታ የሰው ኃይል ለስራ በማሰማራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

ንጋት ኮርፖሬት ካቀፋቸው ኩባንያዎች መካከል በከልቻ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር፣ ጣና ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ አምባሰል የንግድ ስራዎች፣ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ፣ ጣና ኮሙኒኬሽን፣ ዳሽን ቢራ እና ጎንደር ብቅል ፋብሪካ ተጠቃሾች ናቸው።

የንጋት ኮርፖሬት ጠቅላላ ሃብትም እ.ኤ.አ እስከ 2024 መጨረሻ ድረስ 25.2 ቢሊየን ብር መድረሱም ተጠቁሟል።

በ2024 የበጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ ዕውቅናና ሽልማት ከተሰጣቸው ኩባንያዎች መካከል ዋሊያ ቆርኪ ፋብሪካ በአንደኝነት የተዘጋጀለትን ቢዋይዲ ሶንግ ፕላስ የኤሌክትሪክ የቢሮ መኪና የተሸለመ ሲሆን፣ አምባሰል የንግድ ስራዎች ድርጅት በሁለተኛነት የመኪና ተሸላሚ እንዲሁም ጊዮን ፕላስቲክ ፋብሪካ ደግሞ በ3ኛነት የወርቅ ዋንጫ ተሸልሟል።

የንጋት ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አምላኩ አስረስ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ኮርፖሬቱ በአስቸጋሪ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔዎች ውስጥ እያለፈም ውጤታማነት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።

የመሰባሰባችን አላማ ሽልማት ሰጥቶ ለመለያየት ሳይሆን ኩባንያዎቻችን ያስመዘገቡትን ስኬት ማክበርና ከስኬታቸው ትምህርት እንዲወሰድ ለማስተማር ነው ብለዋል፡፡

በዕውቅናና ሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ሽልማቱን የሰጡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው፣ የአማራ ክልል መንግስት የክልሉን ሕዝብ አቅምና ኢኮኖሚ ለማሳደግ እየሠራ ነው ብለዋል።

ንጋት ኮርፖሬት፣ የአማራ ክልል ሕዝብ ሀብት በመሆኑ በቢዝነስ በኢንቨስትመንትና በማህበራዊ ልማት አበረታች አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ኮርፖሬቱ በተለይም በማኑፋክቸሪንግና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀው መንግስትም የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review