AMN-ጥር 7/2017 ዓ.ም
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሀገር እድገት ያላቸውን አስተዋፅኦ በመረዳት መደገፍ እና ችግሮቻቸውን መፍታት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ፡፡
ምክትል ከንቲባና የቢሮ ኃላፊው የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም፣ የሪፎርምና መልካም አስተዳደር ሥራዎችን ገምግመዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሀገር እድገት ያላቸውን አስተዋፅኦ በመረዳት፣ በመደገፍ እና ችግሮቻቸውን በመፍታት ለኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን አቅም ከፍ ማድረግ እንደሚገባ አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን መሠረታዊ ችግሮችን በመፍታት እንደ ሀገር የተያዘውን የእድገት ጉዞ ለማረጋገጥ እና የሀገር ምርትን በመጠቀም በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ላይ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር ማበረታታት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የ“ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ታምርት” ንቅናቄ ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በመተባበር ውጤት እንዲመጣ ከወዲሁ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አቶ ጃንጥራር ማሳሰባቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡