AMN – ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም
በከተማዋ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው እንዲያድግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠንክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በመፍታት ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያስቻለ መጥቷል፡፡
ይህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት ሚናቸውን ያሳደገ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ጥራት እና መጠንም የጨመረ ሆኗል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች የማምረት አቅማቸው ተዳክሞ ከፍ ሲልም ተቋርጦ የነበሩትንም ወደ ምርት እንዲገቡ አስችሏል፡፡
ይህንንኑ ስኬት ከፍ ለማድረግና አሁንም የኢንዱስትሪዎችን ምርታማት ለማሳደግ ንቅናቄው ቀጥሏል፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማም የንቅናቄ መርሀ ግብር ተጀምሯል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎችም ምርቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ካባ መብራቱ በክፍለ ከተማው 486 ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙ ገልጸው በንቅናቄው ኢንዱስትዎችን የመደገፍ እና ችግሮቻቸውን የመፍታ ስራ ተስርቷል ብለዋል፡፡
ንቅናቄውን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በከተማዋ 3 ሺህ 400 በላይ ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እነዚህ እንዱስትሪዎች የማምርት አቅማቸው 60 በመቶ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ኢንዱስትሪዎቹ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ቸግሮቻቸውን የመፍታት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የኢንዱስትሪዎችን ጥያቄ ለመፍታት እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራትም በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ይዞ ለመቅረብ አስችሏል ብለዋል፡፡
ኢንዱስትሪው ለሃገር እድገት እና ኢኮኖሚ የሚያበርክተውን አስተዋጽኦ በመረዳት በቀጣይም አምራች ኢንዱስትሪዎችን የመደገፍ እና ችግሮቻቸውን የመፍታት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡
ምርቶቻቸውን በንቅናቄው ይዘው የቀረቡ የክፍለ ከተማው አመራቾችም ተኪ ምርት በማምረት ለሀገር ኢኮኖሚ አበርከቶ እያደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በቴዎድሮስ ይሳ