አራተኛው የኢትዮ-ኡጋንዳ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በባለሙያዎች ደረጃ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገው ዘርፈ ብዙ ትብብር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
አምባሳደር ዘሪሁን ዛሬ በባለሙያዎች ደረጃ የተጀመረው እና ነገ በሚኒስትሮች ደረጃ የሚካሄደው የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ላቀ ደረጃ እያደገ መምጣቱን አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።
የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የክልላዊ ኢኮኖሚ ትብብር ኃላፊ አምባሳደር ሪቻርድ ቱሙሲሜ ካቦኔሮ በበኩላቸው፣ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ይበልጥ ለማሳደግ ይህ የከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሞያዎች ስብሰባ መካሄድ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
በኡጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዕፀገነት ይመኑ ይህ ስብሰባ እያደገ የመጣውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማላቅ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ባለሙያዎች በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በአቪዬሽን፣ በመከላከያ፣ በቱሪዝም በጤና እና በመሠረተ ልማት፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎችን መከላከል እና በልዩ ልዩ ዘርፎች ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በነገው ዕለት 4ኛው የኢትዮ-ኡጋንዳ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ እንደሚጀመር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።