AMN – ታኅሣሥ 8/2017 ዓ.ም
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ” አሰባሳቢ ገዢ ትርክት ለበለፀገች ኢትዮጵያ ” በሚል መሪ ሀሳብ የኪነ-ጥበብ ምሽት አካሂዷል።
በኪነ-ጥበብ ምሽቱ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ሂሩት ካሣው(ዶ/ር) የኪነ-ጥበብ ስራዎች በማህበረሰቡ ዘንድ የወል ትርክት ፣ ሰላም አንድነትንና ልማትን ለማስረፅ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና፣ ብልፅግና ፓርቲ በርካታ ሰው ተኮር ስራዎችን እና የሚጨበጥ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ሀገሪቱን በአፍሪካ ብሎም በዓለም የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ እየሰራ በሚገኘው ስራ ነጠላ ትርክትን በማስወገድ የወል ገዢ ትርክትን በማስረፅ መስራት ከሁላችን ይጠበቃል ሲሉ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ የሁዋላሸት በቀለ በበኩላቸው ሀገሪቱ ከለውጡ በፊት የተለያዩ ስብራቶች ሲያጋጥሟት መቆየቱን ጠቅሰዉ፣ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ብልፅግና ፓርቲ የመደመር ዕሳቤን ይዞ በመነሳት ሁሉንም በእኩል በማሳተፍ ሁለንተናዊ ዉጤት እያመጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በኪነ-ጥበብ ምሽቱ የክፍለ ከተማው የባህል ቡድን የሙዚቃ፣ የውዝዋዜ፣ የግጥም እና የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ማቅረቡን ከክፍለ ከተማው ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡